በህዳሴ ግድብ ላይ በዋሽንግተን ዲ.ሲ ኢትዮጵያ: ግብጽና ሱዳን ሲያደርጉት የነበረው ውይይት ተጠናቀቀ - ኢዜአ አማርኛ
በህዳሴ ግድብ ላይ በዋሽንግተን ዲ.ሲ ኢትዮጵያ: ግብጽና ሱዳን ሲያደርጉት የነበረው ውይይት ተጠናቀቀ
ጥር 23/2012 (ኢዜአ) በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ በዋሽንግተን ዲ.ሲ. ከጥር 19/2012 ጀምሮ ሲካሄድ የነበረው የኢትዮጵያ: የግብጽና የሱዳን ውይይት ተጠናቋል::
የኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብጽ ልዑካን በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ውሀ ሙሌት እና አለቃቀቅ ዙሪያ በዋሽንግተን ዲሲ ድርድር አካሂደዋል::
የሶስቱ ሀገራት የውጭ ጉዳይ እና የውሃ ሚኒስትሮች እንዲሁም የሕግ እና የውሃ ጉዳይ የቴክኒክ ባለሞያዎችን በድርድሩ የተሳተፉ ሲሆን፣ የአሜሪካ የግምጃ ቤት ኃላፊ እና የአለም ባንክ ተወካዮች በታዛቢነት ተሳትፈዋል፡፡
በድርድሩ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን የውሃ ሙሌት እና አለቃቀቅ በተመለከቱ ጉዳዮች ላይ ትኩረት የተደረገ ሲሆን በድርቅ (Drought)፣ በአመታት የተራዘመ ድርቅ ( prolonged drought ) እንዲሁም በተራዘመ አመታት አነስተኛ የወንዝ ፍሰት (prolonged periods of dry years) ወቅት የሚኖረው የአሞላል ሥርዓት ላይ መሰረታዊ መግባባት መደረሱ ተጠቅሷል፡፡
ስምምነት ያልተደረሰባቸው ቀሪ ጉዳዮች በቀጣይ ውይይቶች መፍትሄ የሚያገኙ ሲሆን የሙሌት እና ውሃ አለቃቀቅ ዝርዝር ረቂቅ ሰነድ እንደሚዘጋጅም ይፋ ተደርጓል፡፡
በሕዳሴው ግድብ የውሃ አሞላል እና አለቃቀቅ ላይ የሚደረገው ድርድር በግድቡ ብቻ ላይ የተወሰነ መሆኑንና የሀገሪቱን ነባር እና የወደፊት በአባይ ወንዝ የመጠቀም መብት በሙሉ የሚያስከብር ማድረግ የኢትዮጵያ መንግስት የማይቀየር አቋም ነው ተብሏል፡፡
በኢትዮጵያ ሕዝብ ገንዘብ እየተሰራ የሚገኘው የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ራስን ችሎ የመልማት መብት እንዲሁም የትብብር መገለጫ ሲሆን መንግስት ግንባታውን አጠናቆ ወደስራ ለማስገባት የሚያደርገው ጥረት የቅድሚያ ትኩረት የሚሰጠው መሆኑ ተብራርቷል፡፡
በ4ቱ ቀናት ቆይታ የተደረገው ውይይት ውጤት የሚመለከት መግለጫ ዛሬ ይወጣል ተብሎ ይጠበቃል ::
ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ በ30 ቀናት ውስጥ የሚጠናቀቅ ለፊርማ የሚሆን ሰነድ በህግ እና በቴክኒክ ሙያተኞች በጥልቀት ተመክሮበት እንዲዘጋጅ ከመግባባት ላይ መደረሱንም አንባሳደር ፍጹም አረጋ እና ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያሳያል፡፡