አገራዊ የለውጥ ሂደቱን ስኬታማ የማድረግ ሥራ ለአንድ ወገን የሚተው አይደለም - ኢዜማ - ኢዜአ አማርኛ
አገራዊ የለውጥ ሂደቱን ስኬታማ የማድረግ ሥራ ለአንድ ወገን የሚተው አይደለም - ኢዜማ
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 22/2012 አገራዊ የለውጥ ሂደቱን ስኬታማ የማድረግ ሥራ ለአንድ ወገን የማይተውና የሁሉንም ተሳትፎ እንደሚጠይቅ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ፓርቲ አስታወቀ፡፡ ፓርቲው ወቅታዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል፡፡ ኢዜማ በመግለጫው እንዳመለከተው፤ በአሁኑ ወቅት ያለውን ፈታኝ ሁኔታ ለማለፍ ሁሉም አካል የራሱን አስተዋጽኦ ማበርከት ይኖርበታል፡፡ አገራዊ ለውጡን በማስቀጠልና ሰላምን በማረጋገጥ በኩል የመንግስት ሚና ትልቅ መሆኑንም አስገንዝቧል፡፡ ኢዜማ በመግለጫው እንዳለው፤ ይህን አስጨናቂ ወቅት ለማለፍ ከባድ ኃላፊነት ወስደው የሚሰሩ አካላት እንዳሉ ሁሉ ግርግር በመፍጠር የራሳቸውን ፍላጎት በኃይል ለመጫን የሚጥሩ ቡድኖችና ግለሰቦችም አሉ፡፡ ''በመሆኑም መንግስት በዜጎች ላይ ችግር ለመፍጠር ሌት ተቀን የሚሰሩና የሚያሴሩትን በቸልታ መመልከት የለበትም'' ብሏል በመግለጫው፡፡ የፖለቲካ አስተሳሰብን በነጻነትና በሰለጠነ መንገድ መግለጽ ዴሞክራሲያዊ መብት መሆኑን ያመለከተው የፓርቲው መግለጫ፤ አገርን የሚያዋርድ ተግባር መፈጸም ለማንም የማይበጅ በመሆኑ ይህን የሚያደርጉ አካላት ከዚህ ተግባራቸው እንዲቆጠቡ አስገንዝቧል፡፡ መንግስት የአገር መገለጫ በሆኑት በህዝብ፣ በሃይማኖት፣ በብሔረሰቦችና በሰንደቅ ዓላማ ላይ የነውር ተግባር የሚፈጽሙትን ለይቶ አስተማሪ የቅጣት እርምጃ እንዲወስድም ኢዜማ ጠይቋል፡፡ “የዴሞክራሲ ግንባታ ሂደቱን መጠበቅ ለሁሉም የሚጠቅም፤ አገርና ህዝብን የሚታደግ ብቸኛ መንገድ ነው” ሲልም ነው በመግለጫው ያመለከተው፡፡ መንግስት የታገቱ የደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን የማስለቀቁን ኃላፊነት በአግባቡ እንዲወጣና የህዝብን ልብ እንዲያሳርፍም ፓርቲው በመግለጫው አሳስቧል፡፡ በተያያዘ ዜና በአንዳንድ የምርጫ ወረዳዎች ፓርቲው ከአመራሮች፣ ከአባላትና ደጋፊዎቹ ጋር ህዝባዊ ውይይቶችን በሚያካሂድበት ወቅት በግለሰቦችና በመንግስት አካላት ችግር እየደረሰብኝ ነው ብሏል፡፡ መንግስት ስርዓት አልበኞችን ስርዓት እንዲያስይዝ፤ የታችኛውን የመንግስት መዋቅርም ሊገመግም እንደሚገባ አሳስቧል፡፡ ኢዜማ አገራዊ ፓርቲ በመሆን ከምርጫ ቦርድ የምስክር ወረቀት ማግኘቱንም ከፓርቲው የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡