የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ ተሳታፊዎች የኢትዮጵያን የለውጥ እንቅስቃሴ ይጎበኛሉ - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ ተሳታፊዎች የኢትዮጵያን የለውጥ እንቅስቃሴ ይጎበኛሉ
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 22/2012 የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ ተሳታፊዎች በኢትዮጵያን ቆይታቸው የተለያዩ የመስብ መዳረሻዎችን እንደሚጎበኙ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት አስታወቀ፡፡ ለጉባኤው ተሳታፊዎች ስለሀገሪቱ የለውጥ እንቅስቃሴ ገለጻ ይደረጋል፡፡ የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ ተሳታፊዎች በቆይታቸው የኢትዮጵያን መድረቀደምት የሚያሳዩ የቱሪስት መዳረሻዎች ይጎበኛሉም ነው የተባለው፡፡ በኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት የማርኬቲንግ ኦፊሰር አቶ ደሳለኝ አበባው ለኢዜአ እንደገለጹት ለአፍሪካ ህብረት የስራ አስፈጻሚዎች እና የመሪዎች ጉባኤ ተሳታፊዎች የኢትዮጵያን የቱሪዝም መዳረሻዎችና የሀገሪቱን የለውጥ ተግባራት ለማስጎብኘት ዝግጅት ተደርጓል፡፡ የጉባኤ ተሳታፊዎች በቆይታቸው የኢትዮጵያን መድረቀደምትነት የሚያሳዩ የቱሪስት መዳረሻዎች ይጎበኛሉ ብለዋል፡፡ የአዲስ አበባና ዙሪያዋን የቱሪስት መዳረሻዎች የሚያስቃኙ መረጃዎች እንደሚሰራጭም አቶ ደሳለኝ ተናግረዋል፡፡ ለእንግዶች ማረፊያና የፕሮቶኮል ጉዳዮችን በተመለከተ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከአዲስ አበባ የሆቴሎች ማህበራት ጋር በጋራ እየሰራ እንደሚገኝም ጠቁመዋል፡፡ ጉብኝት ከሚያደረግባቸው የቱሪዝም መዳረሻዎች መካከል የአንድነት ፓርክ ቀዳሚውን ስፍራ ሲይዝ የእንጦጦና አካባቢው የታሪክ አሻራዎች እንዲሁም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሚገኘው የኢትዮጵያ ጥናት ማዕከል ኢንስቲትዩት በዋናነት ይገኙበታል፡፡ እንደ አፍሪካ ህብረት ባሉ ትላልቅ ሁነቶች ላይ የሚደረጉ የቱሪዝም እንቅስቃሴዎችን የበለጠ ጥቅም ላይ ለማዋል ቱሪዝም ኢትዮጵያ ከአለም ባንክ ጋር በጋራ መሪ ዕቅድ ማዘጋጀቱም ተሰምቷል፡፡ በማስጎብኘት መርሐግብሩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት እና አጋር አካላት ይሳተፉበታል፡፡