በታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ውይይትን ዙሪያ የወጣ የጋራ መግለጫ የለም - አምባሳደር ፍጹም - ኢዜአ አማርኛ
በታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ውይይትን ዙሪያ የወጣ የጋራ መግለጫ የለም - አምባሳደር ፍጹም
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 22/2012 በታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ውይይትን ዙሪያ የወጣ የጋራ መግለጫ አለመኖሩን በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍጹም አረጋ አስታወቁ። በህዳሴው ግድብ ላይ እየተካሄደ ያለው ውይይት ዛሬም መቀጠሉን ገልጸዋል። የኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በኢትዮጵያ ህዳሴ ግድቡ የውሃ አሞላልና አለቃቀቅ ዙሪያ የሚያደርጉ የሶስትዮሽ ውይይት ከጥር 19 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ በዋሺንግተን ዲሲ እየተካሄደ ይገኛል። ውይይቱ እየተካሄደ የሚገኘው አገራቱ ጥር 4 እ 5 ቀን 2012 ዓ.ም በዋሺንግተን ዲሲ የደረሱበትን ስምምነት ለማጠቃለል በያዙት ቀጠሮ መሰረት ነው። የሶስትዮሽ ስብሰባው ባለመጠናቀቁ ከማክሰኞ ወዲህ የወጣ ምንም አይነት የጋራ መግለጫ እንደሌለ በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍጹም አረጋ በትዊተር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል። ውይይቱ ጥር 19 እና 20 ቀን 2012 ዓ.ም እንደሚካሄድ ተገልጾ የነበረ ቢሆንም የአገራቱ የሶስትዮሽ ስብሰባ ዛሬም ለአራተኛ ቀን እንደቀጠለ ገልጸዋል። ኢትዮጵያ በውሃው የመጠቀም መብቷን አሳልፎ የሚሰጥ ምንም አይነት ስምምነት አትፈጽምም ሲሉም አረጋግጠዋል። የሶስትዮሽ ውይይቱ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት፣ አለቃቀቅ እና የድርቅ ወቅት አመራር ላይ ያተኮረ ነው። ኢትዮጵያ በውይይቱ ላይ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው፣ በውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለና ሌሎች ባለሙያዎች ተወክላለች። የአሜሪካ እና የዓለም ባንክ ተወካዮች በታዛቢነት የሚሳተፉበት ውይይት እየተካሄደ የሚገኘው በገንዘብ ሚኒስትሩ ስቴቨን ሙንቺን ጽህፈት ቤት ነው። ጥር 4 እና 5 ቀን 2012 ዓ.ም የኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በዋሺንግተን ዲሲ መወያየታቸው ይታወሳል። ከውይይቱ በኋላ ባወጡት የጋራ አቋም መግለጫ የግድቡ የውሃ ሙሊት ስራ የወንዙን የውሃ መጠን ባገናዘበና የታችኛው ተፋሰስ አገራት ላይ ጉልህ ጉዳት በማያስከትል መልኩ መከናወን እንዳለበት መግባባታቸውን ገልጸው ነበር። በውሃ ሙሌት ጊዜም ሆነ ከሙሌት በኋላ የታችኛው ተፋሰስ አገራት ረዘም ላለ ጊዜ የሚቆይ ድርቅ ቢያጋጥማቸው የወንዙ ፍሰት ምን መምሰል እንዳለበት አገራቱ ተወያይተው መግባባት ላይ ደርሰዋል። የግድቡ አጠቃላይ ሃይል የማመንጨት ስራ የወንዙን የውሃ መጠንና የታችኛው ተፋሰስ አገራት የሚገጥማቸውን የአየር ጠባይ ባገናዘበ መልኩ እንዲከናወን መግባታቸውንም መግለጫው ይፋ አድርጓል። ባለፈው ሳምንት በሱዳን ካርቱም የሶስቱም አገራት የህግ ባለሙያዎች የተወከሉበት ቡድን ስምምነት በተደረሰባቸው የህግ ማዕቀፎች ላይ የጋራ ምክክር ማድረጋቸው የሚታወስ ነው።