ቀጥታ፡

ወጣቱ ትውልድ ባህሉንና ትውፊቱን በበቂ መጠን አለማወቁ በመጤ ባህል እንዲሳብ አድርጎታል

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 22/2012 ወጣቱ ትውል የራሱን ባህልና ትውፊት በበቂ እንዲያውቅ ባለመሰራቱ በመጤ  ባህል ተጽዕኖ ስር እንዲወድቅ ማድረጉን የኢትዮጵያ ባህላዊ ሙዚቃ መምህራን ተናገሩ። አገራዊ ነባር ባህሎችን ለወጣቱ ትውልድ ማስተዋወቅ የሚጠበቅባቸው ተቋማት ጭምር የምዕራባውያን ተጽዕኖ ስር መውደቃቸው ተጠቁሟል። የፈንድቃ ባህል ማዕከል መስራችና የውዝዋዜ አሰልጣኝ አርቲስት መላኩ በላይ እንደሚለው፤ ትውልዱ እራሱን እንዲያውቅና በራሱ የሚኮራ እንዲሆን ያለፈ ታሪኩን ማወቅ አለበት። ተተኪው ትውልድ ያለፈውን ታሪክ፣ ባህልና ቅርስ በአግባቡ ከነአውዳቸው ተረድቶ እንዲጠቀምባቸው ለማስቻል መሰራት እንዳለበትም አስገንዝቧል። አርቲስቱ ባህልና ቅርስን የማስተዋወቅ ሃላፊነቱን ለመወጣትም የተለያዩ ቀደምት  የሙዚቃ ማጫወቻ ሸክላዎችን ወጣቱ እንዲያውቃቸው  በባህል ፌስቲቫል መድረክ ላይ ይዞ መቅረቡን ገልጿል። ''ወጣቱ ባህላዊ የሙዚቃ መሳሪያዎችንም ሆነ ባህላዊ ውዝዋዜዎችን አያውቅም ለማወቅም ፍላጎቱ የለውም ይህ የሆነውም ለባህላዊ ሙዚቃዎች የሚሰጠው ግምት አናሳ መሆን ነው ይላሉ''። በተመሳሳይ መድረክ ላይ በገና፣ ጸናጽል፣ እንቢልታና ነጋሪት የመሳሰሉ ባህላዊ የሙዚቃ መሳሪያዎችን ይዘው የተገኙት የሲሳይ በገና ማሰልጠኛ ተቋም ባለቤት አቶ ሲሳይ ደምሴ በመጤ ባህል ተጽዕኖ ስር ላለመውደቅ በስፋት መሰራት እንዳለበት ገልጸዋል። ባህላዊ የሙዚቃ መሳሪያዎችን ለተተኪው ትውልድ ለማስተዋወቅ የሚመለከታቸው አካላት የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባም ተናግረዋል። አያይዘውም ''ባህላዊ የሙዚቃ መሳሪያ ትምህርት ቤቶች በአገራችን አለመኖራቸውና ያለውን ያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤትን ብንወስድ የምዕራባውያን ባህል የሚቀነቀንበት ነው'' ብለዋል። በመሆኑም ተቋማት ቅድሚያ ለአገራዊ እሴት ቅድሚያ ሊሰጡ እንደሚገባ አስገንዝበዋል። ''አገር በቀል የሙዚቃ መሳሪያዎች ወድቀዋል ትውልዱ በምዕራባውያን ባህል ተስቧል'' ያሉት አቶ ሲሳይ፤ መንግስት ወጣቱ ትውልድ ባህሉን እንዲያውቅ በስፋት መስራት እንዳለበት ተናግረዋል። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የቅርስ ጥበቃ ወመዘክር ሃላፊ መምህር ልሳነወርቅ ደስታ ''አገራችን የበርካታ ቅርሶች፣ የፊደል፣ የስነ ህንጻ መገኛ መሆኗን ለትውልዱ ለማስተዋወቅ እየሰራን ነው'' ብለዋል። ወጣቱ ትውልድ የአገሩን ባህል፣ ታሪክና ትውፊት ባለማወቁና በመጤ ባህል በመወረሱ ለአገር አንድነት ያለው ትኩረት መቀነሱን ጠቁመው፤ ''ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገሪቱ እየታየ ያለው የሰላም ዕጦት ወጣቱ ባህሉንና ታሪኩን ባለማወቁና በሌላ ባህል በመወረሱ ነው'' ብለዋል። በመሆኑም ተተኪው ትውልድ የአገር ፍቅር እንዲኖረውና ተከባብሮና ተዋዶ እንዲኖር እንዲሁም ባህሉን አውቆ በራሱ የሚተማመን እንዲሆን ሁሉም የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጥሪ አስተላልፈዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም