የስደት አስከፊነት ላይ ትኩረቱን ያደረገ የሙዚቃ ውድድር ተካሄደ - ኢዜአ አማርኛ
የስደት አስከፊነት ላይ ትኩረቱን ያደረገ የሙዚቃ ውድድር ተካሄደ
አዲስ አበባ፣ጥር 22/2012 ዓ/ም (ኢዜአ) አሳሳቢ ደረጃ ላይ የደረሰውን የስደት አስከፊነት ማስተማር ላይ ትኩረቱን ያደረገ የሙዚቃ ውድድር ትናንት ማምሻውን በጣሊያን የባህል ተቋም ተካሄደ። በውደድሩ ወቅት ሕገ-ወ ስደት የሚያስከትለዉን ጉዳት ለማስገንዘ ሙዚቃ የጎላ አስተዋፅኦ እንዳለዉ ተገልጿል። ''በህገ-ወጥስደት ስጋቶች ላይ አዲስ የዜማ ቅኝት'' በሚል ጭብጥ 'ስደት ለምን' በሚል ርዕስ በዳዊት ንጋቱ፣ ኑሩ ኡመርና ተስፋዬ ማሞ የተዘጋጀው ሙዚቃ አሸናፊ ሆኗል። የውድድሩ የመጀመሪያ አሸናፊዎችም ሽልማታቸውን በኢትዮጵያ የጣሊያን አምባሳደር አርቱሮ ሉዚ ተቀብለዋል። የጣሊያን ባህል ማዕከል ከአዉሮፓ ኅብረት ጋር በመተባበር ሕገ-ወጥስደት የሚያስከትለዉን ጉዳት ግንዛቤ ለመስጠት በተዘጋጀው ውድድር ላይ ዘጠኝ ተወዳዳሪዎች ቀርበው ነበር። ባህል ማዕከሉ ባደረገዉ የሙዚቃ ዉድድር ላይ የተገኙት የጣሊያኑ አምባሳደር አርቱሮ ሉዚ እንደገለፁት፤ ትልቅ ተመልካች ባለበት ሙዚቃን በመጠቀም ስለሕገወጥ ስደት መልዕክት ማስተላለፍ መቻሉ አደጋዉን ለማሳየት ይረዳል። የኢትዮ-ጃዝየሙዚቃ አባት ሙላቱ አስታጥቄን ጨምሮ ድምፃዊ ናርዶስ ተስፋዉና ሙዚቀኛ ዐቢይ ወልደማርያም ዉድድሩን ዳኝተዋል። ለአሸናፊዎቹ የገንዘብ ሽልማት ተበርክቷል።