በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማእከል ለ3 ቀናት የሚቆይ የባህል ፌስቲቫል ተከፈተ

አዲስ አበባ፣ ጥር 22/2012 (ኢዜአ) በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማእከል ለሶስት ቀናት የሚቆይ የባህል ፌስቲቫል ተከፈተ። የአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ የባህል ዘርፍ ሃላፊ ሰርጸፍሬ ስብሃት እንዳሉት የፌስትቫሉ አላማ  ባህልንና እሴቶችን ለተተኪው ትውልድ ለማስተዋወቅ ነው። በመሆኑም በዝግጅቱ ላይ ብዝሃ ባህልና ኪነ ጥበብን የሚያሳዩ የመድረክ ክዋኔዎች፣ የዕደ ጥበብ ውጤቶች እንዲሁም የፓናል ውይይቶች ይካሄዳሉ ብለዋል። በዝግጅቱ ላይ የሚገኙ ተማሪዎች፣ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች እየተዝናኑ ባህልና እሴቶችን በቅጡ እንደሚረዱም እናምናለን ነው ያሉት። የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የባህል ዘርፍ ዋና አማካሪ ዶክተር እልፍነሽ ሃይሌ እንዳሉት የባህል ፌስቲቫሉ ባህልና የታሪክ እሴቶችን ለቀጣዩ ትውልድ ለማሻገር ከፍ ያለ ፋይዳ አለው። ዜጎች ስለአገራቸው ታሪክ፣ ባህል፣ ወግ እና ልማድ ተጨማሪ እውቀት እንዲኖራቸውም ያግዛል ብለዋል። በዝግጅቱ ላይ የተለያዩ ባህላዊ አልባሳትን የሚያስተዋውቅ፣ ታሪካዊ ቦታዎችን በምስል የሚያሳይ መርሃ ግብር መኖሩንም ጠቁመዋል። የቱሪዝም ኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር አቶ ስለሺ ግርማ በበኩላቸው ፌስቲቫሉ አንድነትን፤ አብሮነትን የሚዘክሩ የአኗኗር ጥበቦችን ካለፈው ታሪካችን የምናውቅበት እንዲሁም ለተተኪው ትውልድ የምናስተላልፍበት አጋጣሚ ነው ብለዋል። በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማእከል የሚካሄደው 11ኛው የባህል ፌስቲቫል ''ባህልና ኪነ ጥበብ ለህዝቦች ሰላምና ሀገራዊ አንድነት'' በሚል  መሪ ሃሳብ ለሶስት ቀናት ይቆያል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም