ቀጥታ፡

የሴቶች ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ ከነገ በስቲያ ይጀመራል

አዲስ አበባ፤ ጥር 22/2012( ኢዜአ) የሐበሻ ሲሚንቶ የሴቶች ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ የፊታችን እሑድ በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም ይጀመራል።

በሊጉ ውድድር ብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ፣ ፌዴራል ማረሚያ ቤቶች፣ ጌታዘሩ ስፖርት ክለብና ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ይሳተፋሉ።

የመጀመሪያ ሳምንት ጨዋታዎች ከነገ በስቲያ በሚካሄዱ ጨዋታዎች ይጀመራል።

በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም ከጠዋቱ 2 ሠዓት ከ30 ብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካና ፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ሶዶ ላይ ከቀኑ በ9 ሠዓት ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ከጌታዘሩ ስፖርት ክለብ ጋር ይጫወታል።

ክለቦቹ ከታህሳስ 22-25 ቀን 2012 ዓ.ም ለሊጉ ዝግጅት እንዲረዳቸው በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም የአቋም መለኪያ ውድድር አድርገው ብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካን አሸንፏል።

ብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካና ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ አዲስ የተቋቋሙ ክለቦች ሲሆኑ በአንጻሩ የኢትዮጵያ ውሃ ስራዎች ባለፈው ዓመት ክለቡን ማፍረሱ ይታወሳል።

ለሴቶች የቮሊቦል ክለቦች ቁጥር ማነስ ተተኪ ታዳጊ ወጣቶች አለመፍራታቸውና ግለሰቦችና ድርጅቶች ለክለቦች ያላቸው ፍላጎት እምብዛም መሆን እንደሆነ የስፖርቱ አፍቃሪዎች ይገልጻሉ።

አዲሶቹ ብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካና ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የሴቶች ክለቦች መነቃቃት እንደሚፈጥሩና ሌሎችም ክለብ በማቋቋም ለስፖርቱ እድገት እንዲሰሩ የቮሊቦል ፌዴሬሽን ጥሪ አቅርቧል።

የሴቶች የቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ ክለቦች የውድድር አማራጭ በማስፋት በተያዘው ዓመት የጥሎ ማለፍ ውድድርና አገር አቀፍ ሻምፒዮና እንደሚካሄድም አስታውቋል።

በተያያዘ በሐበሻ ሲሚንቶ የወንዶች ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ ተስተካካይ ጨዋታ ከነገ በስቲያ የሚካሄድ ሲሆን ሶዶ ላይ ከጠዋቱ በ3 ሠዓት ወላይታ ድቻ ና መከላከያ ይጫወታሉ።

በሌላ ዜና የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ አምስተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ነገና ከነገ በስቲያ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ይካሄዳሉ።

በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ከፌዴራል ፖሊስ፤ ቦንጋ ላይ አዲሱ የሊጉ ተሳታፊ ሚዛን አማን ከተማ ከከምባታ ዱራሜ በተመሳሳይ ከጠዋቱ 3 ሠዓት ላይ ይጫወታሉ።

ከነገ በስቲያ በክልል ከተሞች ሶስት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።

ጎንደር ላይ ጎንደር ከተማ ከኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ፣ መቐለ ላይ መቐለ ሰብዓ እንደርታ ከፌዴራል ማረሚያ ቤቶችና ቡታጅራ ላይ ቡታጅራ ከተማ ከመከላከያ በተመሳሳይ ከጠዋቱ በ3 ሠዓት ይጫወታሉ።

የፕሪሚየር ሊጉን የደረጃ ሰንጠረዥ መቐለ ሰብዓ እንደርታና ቂርቆስ ክፍለ ከተማ በተመሳሳይ 8 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው በቅደም ተከተል አንደኛና ሁለተኛ ደረጃን ሲይዙ ኮልፌ ቀራኒዮ በ6 ነጥብ 3ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

አዲሱ የሊጉ ተሳታፊ ሚዛን አማን ከተማ ያለ ምንም ነጥብ የመጨረሻውን 10ኛ ደረጃ ይዟል።

በተጨማሪም የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፕሪሚየር ሊግ የአንደኛ ሳምንት ተስተካካይ ጨዋታዎች ከነገ በስቲያ በክልል ከተሞች ይካሄዳሉ።

በሴቶች ጎንደር ላይ ጎንደር ከተማ ከወልቂጤ ከተማ  እና ጅማ ላይ አዲሱ የሊጉ ተሳታፊ ጅማ ከተማ ከአማራ መንገድና ህንጻ ዲዛይን ጋር በተመሳሳይ ከጠዋቱ 3 ሠዓት ላይ ይጫወታሉ።

በወንዶች ውቅሮ ላይ አዲሱ የሊጉ ተሳታፊ አጋዚ ውቅሮ ከየካ ክፍለ ከተማ ከጠዋቱ 3 ሠዓት እንዲሁም ጎንደር ላይ ጎንደር ከተማ ከወልቂጤ ከተማ ከረፋዱ በ4 ሠዓት የሚጫወቱ ይሆናል።

ጨዋታዎቹ በመጀመሪያ ሳምንት ያልተካሄዱት ክለቦች ገጠመን ባሉት የፋይናንስ ችግር ምክንያት በመራዘማቸው እንደሆነ የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።

የቅርጫት ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ሁለተኛ ሳምንቱ ላይ የደረሰ ሲሆን የሶስተኛ ሳምንት ጨዋታዎች በቀጣዩ ሳምንት የሚካሄዱ ይሆናል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም