ቀጥታ፡

ጎረቤቱ እየተከፋ ደስተኛ ሊሆን የሚችል የለም... የሃይማኖት አባቶች

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 22/2012 ''ጎረቤቱ ሲደሰት የሚደሰት፣ ሲከፋ አብሮ የሚከፋ እንጂ ጎረቤቱ ሲከፋ ደስተኛ ሊሆን የሚችል የለም'' በማለት የሃይማኖት አባቶች ተናገሩ።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የተለያዩ እምነት አባቶች እንደገለጹት፤ ከደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ወጥተው ወደ ቤተሰቦቻቸው ሲያቀኑ የታገቱ ተማሪዎች ቤተሰቦች እንባ እና ሃዘን የሁሉም ኢትዮጵያዊ ሀዘን ነው።

''ድርጊቱ የሚያሳዝንና የሚወገዝ ድርጊት ነው''ያሉት የሃይማኖት አባቶቹ፤ ''ከኢትዮጵያዊነት ያፈነገጠ ተግባር መፈጸሙ ለድርጊቱ ፈጻሚዎች ደስታ የማያስገኝ፤ ለሌሎችም ትርፍ የማያመጣ ነው'' ብለዋል።

እገታ የተፈጸመባቸውን ተማሪዎች ለማስለቀቅ ሁሉም ሊተባበር እንደሚገባ አመልክተው፤ መንግስትም ጉዳዩ አፋጣኝ እልባት እንዲያገኝ እንዲሰራ መክረዋል።

ህዝቦቿ በሰላምና በፍቅር ተሳስበው በሚኖሩባት ኢትዮጵያ እንዲህ አይነት ድርጊት እየተፈጸመ አገራዊ መልካም እሴትን እንዳያጠፋ መንግስት ተገቢውን እርምጃ መውሰድ እንደሚገባውም ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስቲያን የመንበረ ፓትሪያርክ ጠቅላይ ጽህፈት ቤት የትንሳኤ ማሳተሚያ ድርጅት ስራ አስኪያጅ ንቡረእድ ኤልያስ አብርሃ ድርጊቱ ዘግናኝና አሳፋሪ ና አግዜያብሄርንም እናመልካለን ከሚል  ሰው አይጠበቅም ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ጽህፈት ቤት ሼክ መሐመድ ሲራጅ በበኩላቸው አሁን የሚታየው ድርጊት አሳፋሪ ከመሆኑ በተጨማሪ  ጎረቤትህ ተከፍቶ አንተ ልትደሰት አትችልም ይበልጡኑም  አላህን ያሳዘነ በመሆኑ ሊወገዝ ይገባዋል ነው ያሉት፡፡

ዶክተር ኤርሚያስ ማሞ የኢትዮጵያ ቃለ ህይወት ቤተ ክርስቲያን ምክትል ዋና ጸሃፊ

እኔ ልጆች አሉኝ የኔ ታግተው ቢሆን እንቅልፍ አይወስደኝም የሁሉን እንደራሴ ነው የሚሰማኝ  መንግስትም ይሄን ድርጊት በተገቢው በመለየት እርምጃ መውሰድ አለበት እኛም ድርጊቱን ማውገዝ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

እንደ ሃይማኖት አባቶቹ ገለጻ፤ የተለያየ ሃሳብ የሚያራምዱ አካላት ተቀራርበው ልዩነታቸውን ለመፍታት መስራት ይኖርባቸዋል።

መንግስት የህግ የበላይነትን የማስከበር ሃላፊነቱን መወጣት እንደሚጠበቅበት አመልክተው፤ መጥፎና አደገኛ አካሄዶችን ለመከላከል ከሁሉም አካላት ጋር ተቀናጅቶ ሊሰራ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ስርዓት አልበኝነትን ለመቆጣጠር ተመጣጣኝ እርምጃ መወሰድ እንዳለበትም ጠቁመዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ከፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽንና ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመሆን በታገቱት ተማሪዎች ዙሪያ በሰጠው መግለጫ ታጋቾቹን ለማስለቀቅ የምርመራ ቡድን በማቋቋም እየተሰራ ነው።

የምርመራ ሂደቱ ሲጠናቀቅም ተጨባጭ መረጃ ለህዝቡ ይፋ እንደሚሆን አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም