የግብጽ ኮፕቲክ ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ልዑካንን ተቀብለው አነጋገሩ - ኢዜአ አማርኛ
የግብጽ ኮፕቲክ ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ልዑካንን ተቀብለው አነጋገሩ
ጥር 21 ቀን 2012 ( ኢዜአ) የግብጽ ኮፕቲክ ቤተርክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ታውድሮስ ሁለተኛ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ልዑካንን ተቀብለው አነጋግረዋል። ታውድሮስ ሁለተኛ የቤተ ክርስቲያኑ ዋና መቀመጫ በሆነችው የካይሮ አባሲያ በሚገኘው የቅዱስ ማርቆስ የኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ካቴድራል ልዑካን ቡድኑን ተቀብለው አነጋግረዋል። የግብጹ የዜና ወኪል ሜና የኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ቃል አቀባይን ዋቢ አድርጎ እንደዘገበው የሁለቱ ቤተክርስቲያናት ሃላፊዎች ቤተክርስቲያናቱ ለረጅም ዘመናት ባላቸው ግንኙነት ዙሪያ ምክክር አድርገዋል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትሪያሪክ ሊቀጳጳስ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ አማካሪ አባ ገብረየሱስ ወልደኪዳን የምስራቅ ሸዋ አገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ በውይይቱ ላይ ተሳትፈዋል። የኮፕቲክ ቤተክርስቲያን የመካከለኛው ምስራቅ ጉዳዮች ተወካይ ሃላፊ ገርጊስ ሳለህ እና አቡነ አንጄሊዎስ አልነቃዲ በውይይቱ ላይ ተገኝተዋል። ታውድሮስ ሁለተኛ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ልዑካንን ተቀብለው በማነጋገራቸው መደሰታቸውን ገልጸው ሁለቱ ቤተክርስቲያናት ያላቸውን አንድነት ማጠናከር ያስፈልጋል ብለዋል። የአስተሳሰብ ልዩነቶቻችን ወደ ጎን በመተው የኮፕቲክ ቤተክርስቲያናት ለክርስትና እምነት ተከታዮች አንድነት በጋራ መስራት እንደሚገባቸውም ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ልዑካን በቅዱስ ማርቆስ የኮፕቲክ ኦርቶክስ ካቴድራል ከግብጽ፣አርሜኒያና ሶሪያ ኮፕቲክ ቤተክርስቲያናት የሃይማኖት አባቶች ጋር በካቴድራሉ የጸሎት ስነ ስርዓት ላይ መሳተፋቸውን ዘገባው ያመለክታል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንና የግብጽ ኮፕቲክ ቤተክርስቲያን ከ4ኛው ክፍለ ዘመን የመጀመሪያ አጋማሽ ጀምሮ ለረጅም ክፍለ ዘመናት የቆየ ግንኙነት አላቸው።