ቢቢሲ ለማህበረሰብ መገናኛ ብዙሃን ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ ቀረበ - ኢዜአ አማርኛ
ቢቢሲ ለማህበረሰብ መገናኛ ብዙሃን ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ ጥር 20/2012 ( ኢዜአ) በኬንያ ናይሮቢ መቀመጫውን ያደረገው የቢቢሲ ምስራቅ አፍሪካ ቢሮ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ለሚገኙ አገር በቀል የማህበረሰብ መገናኛ ብዙሃን አቅም ግንባታ ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ ቀረበ። በኬንያ የኢፌዲሪ አምባሳደር መለስ ዓለም በናይሮቢ የሚገኘውን የቢቢሲ የምስራቅ አፍሪካ ቢሮ ዛሬ ጎብኝተዋል። በጉብኝታቸውም ከሚዲያ ተቋሙ የስራ ኃላፊዎች፣ አርታኢያንና የረዥም ጊዜ ልምድ ካካበቱ ጋዜጠኞች ጋር በኢትዮጵያ ገጽታ እና ኢትዮጵያን በተመለከቱ ጉዳዮች ላይ ሚዛናዊ ዘገባዎች ተደራሽ በሚደረጉበት ሁኔታ ላይ ተባብሮ ለመስራት ምክክር አድርገዋል። አምባሳደር መለስ እንዳሉት፤ እንደ ቢቢሲ ያሉ አንጋፋና ተፅዕኖ ፈጣሪ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት በኢትዮጵያ ያሉ የማህበረሰብ መገናኛ ብዙሃን አቅም በመገንባትና ጥራታቸውን በማሳደግ በኩል የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ ይገባል። የቢቢሲ ምስራቅ አፍሪካ ቢሮ በአማርኛ፣ በትግርኛ፣ በአፋን ኦሮሞና በሶማልኛ ቋንቋዎች የተለያዩ መረጃዎችን ለህዝቡ ተደራሽ በማድረግ የስርጭት አድማሱን በማስፋቱ አምባሳደር መለስ ምስጋና አቅርበዋል። ኢትዮጵያ በቀጣናውም ሆነ በተለያዩ የዓለም አቀፍ መድረኮች ካላት ተደማጭነትና ተፅዕኖ ፈጣሪነት እንዲሁም ካላት ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር፣ የቋንቋና የባህል ብዝሃነት አንፃር የመገናኛ ብዙሃኑ በአሁኑ ወቅት የሰጠውን አጭር የአየር ጊዜ እንዲያራዝምና በሌሎች የኢትዮጵያ ቋንቋዎችም መረጃዎችን እንዲያሰራጭ ጠይቀዋል። በመጨረሻም በቀጣዩ አገራዊ ምርጫ ቢሮው ሚዛናዊና እውነትን መሠረት ያደረጉ ዘገባዎችን እንዲያሰራጭም አምባሳደር መለስ ጥሪ አቅርበዋል።