ቀጥታ፡

በግማሽ ዓመቱ ከውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት 1 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ተገኘ

ጥር 20/2012 (ኢዜአ) በበጀት ዓመቱ አጋማሽ ከውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት አንድ ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ዶላር መገኘቱን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ገለጸ። በግማሽ ዓመቱ ለማግኘት ታቅዶ የነበረው ሁለት ቢሊዮን ዶላር ሲሆን የዕቅዱን 70 በመቶ መፈፀም ተችሏል። ኢትዮጵያ ለውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ተመራጭ ከሆኑ ጥቂት የአፍሪካ አገራት በግንባር ቀደምትነት ትጠቀሳለች። የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ መኮንን ኃይሉ ለኢዜአ እንደገለጹት የኢንዱስትሪ ፓርኮች መስፋፋትና ምቹ የኢንቨስትመንት ፖሊሲው ባለሃብቶች መዕዋለ ንዋያቸውን እንዲያወጡ ዕድል ፈጥሯል። ለግማሽ ዓመቱ ዕቅድ ሙሉ በሙሉ አለመሳካት በአገሪቷ አንዳንድ አካባቢዎች የነበረው ያለመረጋጋት፣ የውጭ ምንዛሬና የኤሌክትሪክ ኃይል እጥረት ምክንያቶች መሆናቸውን አስረድተዋል። በቀሪው ግማሽ ዓመት በተለይም የመንግስት የልማት ድርጅቶችን ወደ ግል የማዛዋሩ ሂደት ወደ ተግባር የሚገባ በመሆኑ በርካታ የውጭ ባለሃብቶች እንደሚመጡ ይጠበቃል ብለዋል። ኮሚሽኑ በአንዳንድ አካባቢዎች የፀጥታው ሁኔታ እንዲረጋጋ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየሰራ ይገኛል። ይህም በቀሪው ጊዜ የተሻለ ሠላምና መረጋጋት በመፍጠር የኢንቨስትመንት ፍሰቱን የበለጠ ለማሳደግ እንደሚያስችል አቶ መኮንን ገልጸዋል። ከተለያዩ አገራት የሚመጡ ባለሃብቶች በማምረቻ ኢንዱስትሪ፣ በግብርና፣ በጨርቃጨርቅና አልባሳት፣ በምግብ ማቀነባበርና ሆቴልና ቱሪዝምን ጨምሮ በተለያዩ መስኮች እየሰሩ መሆኑንም ተናግረዋል። በበጀት ዓመቱ ከውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት አራት ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው በቀሪው ጊዜ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ርብርብ ይደረጋል ብለዋል። የመንግስታቱ ድርጅት እ.አ.አ 2019  በ"ኢንቨስትመንት ትሬንድስ ሞኒተር" ይፋ ባደረገው ሪፖርት የአገሪቷ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መጠን ከ3 ነጥብ 2 ቢሊዮን ወደ 2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ዝቅ ማለቱን አመላክቷል። ይሁንና ሪፖርቱ የአገሪቷን ቀጥታ የኢንቨስትመንት መጠን የማይገልጽና ከእውነት የራቀ መሆኑን ነው ኮሚሽኑ ያስተባበለው። ለዚህ እንደ ማሳያ ያስቀመጠው ደግሞ ባለፉት ሁለት ዓመታት የተመዘገበውን የኢንቨስትመንት መጠን ነው። በ2010 ዓ.ም 3 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር፣ በ2011 ዓ.ም ደግሞ 3 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር ከውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መገኘቱን ነው ኮሚሽኑ የገለጸው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም