የተሻለች ኢትዮጵያን ለመፍጠር ትውልዱን የሚያንፅ ጠንካራ ሥርዓተ ትምህርት ሊኖር ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የተሻለች ኢትዮጵያን ለመፍጠር ትውልዱን የሚያንፅ ጠንካራ ሥርዓተ ትምህርት ሊኖር ይገባል
አዲስ አበባ ጥር 20/2012 ( ኢዜአ) የተሻለች ኢትዮጵያን ለመፍጠር ትውልዱን ከታች ጀምሮ የሚያንፅ ጠንካራ ሥርዓተ ትምህርት ሊኖር እንደሚገባ ተገለጸ። የአገር ግንባታ ከየት ይጀምራል? በአገር ግንባታ ላይ የትምህርት ተቋማት ሚና ምን ይሁን? በሚሉት ሃሳቦች ላይ ያተኮረ ውይይት በአዲስ አበባ ተካሂዷል። የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ባዘጋጀው ውይይት ምሁራንና የትምህርት ተቋማትና የተለያዩ የሙያ መስኮች ተወካዮች ተሳትፈውበታል። የትምህርት ተቋማት ከባህል፣ ከአገራዊ ማንነትና ሥነ ምግባር አንጻር የት ላይ ናቸው? በቀጣይ የተሻለች አገር ለመፍጠርስ ምን ይደርግ? በሚሉት ጉዳዮችም የውይይት መነሻ ሀሳብ በምሁራን ቀርበው ተመክሮባቸዋል። ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የተወከሉት ፕሮፌሰር ያለው እንዳወቅ ባቀረቡት የውይይት መነሻ ሀሳብ እንዳሉት በኢትዮጵያ የተማሪዎችን ስነ-ልቦና የሚረዳ ስርዓተ ትምህርት አለመኖር ውጤታማ የሰው ኃይል እንዳይፈጠር እያደረገ ነው። የትኛው ተማሪ ምን አይነት ዝንባሌ አለው? በየትኛው መስክ ቢሰማራ ውጤታማ ይሆናል? የሚሉ ጉዳዮች ከግምት ውስጥ አለመግባታቸው ችግር መፍጠሩንም ጠቅሰዋል። እንደ ፕሮፌሰር ያለው ገለጻ በኢትዮጵያ የሚሰጠው ትምህርት ሙያዊ፣ መንፈሳዊና አዕምሯዊ ዕድገትን ማምጣት በሚያስችል መልኩ ሊቃኝ ይገባል። ''አሁን ያለው ስርዓተ ትምህርት የተማሪዎች የሥራ ባህል ማጎልበትና የአገር ፍቅር ላይ ክፍተት አለበት'' ያሉት ፕሮፌሰሩ የሥርዓተ ትምህርት ቀረጻው መሰል ጉዳዮች ላይ ቢያተኩር ለአገር ግንባታ አስተዋጽኦ የሚያበርክት ጠቃሚ ትውልድ ለመፍጠር ያግዛል ብለዋል። በውይይቱ ላይ ተማሪዎች የተሻለች አገር የመፍጠር ስራውን እንዲያግዙ በቅድሚያ ባህላቸውን በወጉ እንዲያውቁ ማድረግና የማንነታቸውን ሥነ ምግባር እንዲላበሱ ማድረግ ቁልፍ ጉዳይ እንደሆነ ተነስቷል። ትውልድ የማነጽ ትልቅ ሚና ያላቸው መምህራንም ባህላቸውን ጠንቅቀው ማወቅ፤ ያወቁትንም ለተማሪዎቻቸው ለማስተላለፍ ዝግጁ መሆን ይጠበቅባቸዋል ነው የተባለው። ከኢትዮጵያ ጥናት ተቋም የመጡት አህመድ ዘካሪያ በኢትዮጵያ ያለው ስርዓተ ትምህርት በአገር በቀል እውቀቶች ያልተቃኘ በመሆኑ ስለ አገሩ ሙሉ ግንዛቤ ያለው ትውልድ እንዳይፈጠር አድርጓል ይላሉ። ''ቀድሞ የነበረው ትምህርት ስነ-ምግባር ላይ ያተኮረና ተማሪዎች ባህልና ወጋቸውን በአግባቡ እንዲረዱ የሚያደርግ ነበር" ያሉት ደግሞ የውይይቱ ተሳታፊ አቶ ውበቱ ወርቄ ናቸው። "አሁን ከትምህርት ጥራት ይልቅ ለሽፋን ቅድሚያ ተሰጥቷል" የሚል ሀሳብ የሰነዘሩት አቶ ውበቱ የአገሪቷን ባህል፣ አኗኗርና መስተጋብር ከግምት ያስገባ አዲስ ስርዓተ ትምርት እንደሚያስፈልግ አጽንኦት ሰጥተዋል።