ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመግታት ትኩረት ይሻል - ኢዜአ አማርኛ
ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመግታት ትኩረት ይሻል
ጥር 20/2012 ( ኢዜአ) ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር በዜጎች ላይ ጉዳት እየደረሰ በመሆኑ ለመግታት ትኩረት እንዲሰጠው በአማራ ክልል መተማና ቃሉ ወረዳ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ነዋሪዎች ጠቆሙ። በክልሉ በግማሽ ዓመቱ በህገ ወጥ መንገድ ከሃገር ለመውጣት ሲሞክሩ የተደረሰባቸው 4 ሺህ 500 ወጣቶች ተይዘዋል። በምዕራብ ጎንደር ዞን መተማ ዮሐንስ ከተማ ነዋሪ አቶ ተስፋሁን ፈጠነ እንዳሉት ወደ ውጭ ለመውጣት ከሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ብዛት ያላቸው ወጣቶች ወደ መተማ ይመጣሉ። እነዚህ ዜጎች መተማ ከተማ ከደረሱ በኋላ በማታለል ይዘዋቸው ያመጧቸው ህገ ወጥ አዘዋዋሪዎች ጥለዋቸው ስለሚሰወሩ ለእንግልት ሲዳረጉ ይሰተዋላል። "ከህገ ወጥ ተዘዋዋሪዎቹ አብዛኞቹ ወጣት ሴቶች ናቸው "ያሉት አቶ ተስፋሁን ልጃገ ረዶቹ ሳይወዱ ወደ ሴተኛ አዳሪነት እየገቡ ህይወታቸው እየተበላሸ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ መንግስት የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት ህገወጥ የሰዎች ዝውውር ለመግታት ትኩረት እንዲሰጠው ጠቁመዋል። በደቡብ ወሎ ዞን ቃሉ ወረዳ የደጋን ከተማ ነዋሪ አቶ ሰይድ ሁሴን በበኩላቸው "በደላሎች መሪነት በደጋንና ባቲ ከተሞች አቋርጠው በአፋር በኩል ወደ አረብ ሃገራት ለመሻገር የሚሞክሩ ወጣቶች በርካታ ናቸው " ብለዋል፡፡ አስተያየት ሰጪው እንዳመለከቱት በየጊዜው በአካባቢው ጫካንና ጨለማን ተገን አድርገው የሚሄዱና በኮንቲነር ጭምር ተጭነው ለማለፍ ሲሞክሩ በፖሊስ የሚያዙ ቁጥራቸው ከፍ ያለ ነው። በጉዞ ላይ በሚገጥማቸው እንግልትም ህይወታቸው እስከ ማለፍ እንደሚደርስ የተመለከቱበት አጋጣሚ እንደነበርም ተናግረዋል። በዜጎች ላይ እየደረሰ ያለውን ጉዳት ለመቀነስ በየደረጃውያለው የመንግስት አካል ትኩረት እንዲሰጠው ጠቁመዋል። በክልሉ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ የሰው ኃይል ጥናትና የስራ ስምሪት ማስፋፊያ ዳይሬክተር አቶ ጌታሰው መንጌ እንደገለጹት በደላሎች ተታለው ከሃገር ለመውጣት የሚጥሩ ወጣቶች ቁጥር ተበራክቷል። የህገ ወጥ ስደት አስከፊነት ግንዛቤ ለመፍጠር ጥረት ቢደረገም ለመግታት አስቸጋሪ መሆኑን ገልጸዋል። ባለፉት ስድስት ወራት በህገወጥ መንገድ ወደ ውጭ ለመውጣት ሲሞክሩ የተደረሰባቸው 4ሺህ 543 ወጣቶች ተይዘው ወደ ቤተሰቦቻቸው እንዲመለሱ ተደርጓል። ሆኖም አሁንም መጨመሩን አመልክተው ከወቅታዊ ችግር ጋር በተያያዘ በየአካባቢው በቂ የስራ ዕድል አለመፈጠር ጉዳዩን አስቸጋሪ እንዳደረገው ገልፀዋል። ለመከላከል የተቋቋመው የመከላከልና የህግ ማስከበር ግብረ ኃይሉም ጉዳዩን እየገመገመ በማስተካከል በኩል ክፍተት እንዳለበት ጠቁመዋል። "በበጀት እጥረት ምክንያት የህገ ወጥ ሰዎች ዝውውር ስራ መስራት አልተቻለም" ያሉት ደግሞ በክልሉ ጠቅላይ አቃቤ ህግ የህገወጥ የሰዎች ዝውውር መከላከል አስተባባሪ አቶ ታደሰ ሙላት ናቸው። አስተባባሪው አንዳሉት ባለው አቅም በተደረገው ጥረት 52 ደላሎች መያዛቸውን ጥቅሰው፤ ከእነዚህም አስሩ ተከሳሽና ማስረጃ ባለመቅረቡ በነፃ ሲሰናበቱ ቀሪዎቹ ጉዳያቸው በፍርድ ሂደት ላይ ይገኛል። በቀጣይ ያለባቸውን ችግር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተነጋግረው በመፍታት ህገ ወጥ ድርጊቱን ለመግታት ጥረት እንደሚያደርግ አስረድተዋል።