ራያ ዩኒቨርስቲ የመስህብ ስፍራዎችን ለቱሪዝም አገልግሎት ለማዋል እየሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ራያ ዩኒቨርስቲ የመስህብ ስፍራዎችን ለቱሪዝም አገልግሎት ለማዋል እየሰራ ነው
ማይጨው /ኢዜአ/ ጥር 20 ቀን 2012 ራያ ዩኒቨርስቲ በትግራይ ደቡባዊ ዞን የሚገኙ የመስህብ ስፍራዎችን ለቱሪዝም አገልግሎት እንዲውሉ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ገለፀ ። በዩኒቨርስቲው የጂኦግራፊ መምህርና የቱሪዝም ተመራማሪ መምህር ደባሲ ግደይ ለኢዜአ እንደገለጹት በዞኑ እምቅ የተፈጥሮ ሀብት ቢኖርም እስከ አሁን ድረስ ለቱሪዝም አገልግሎት ማዋል አልተቻለም ። ‘’የቱሪዝም ሀብቶችን በሚፈለገው ደረጃ ባለመልማታቸውና እንዲተዋወቁ ባለመደረጉ የአካባቢው ማህበረሰብ ይሁን አገሪቷ ከዘርፉ ማግኝት የሚገባትን ጥቅም እያገኘት አይደለችም’’ብለዋል። ዩኒቨርስቲው በዞኑ የሚገኙ ተፈጥሯዊ እና ባህላዊ መስህቦችን በጥናት በመለየት ወደ ሀብትነት የሚቀየሩበት መንገድ እያመቻቸ መሆኑን ተናግረዋል። ጎብኚዎች የፈለጉትን ቦታ ለመጎብኘት እንዲረዳቸው የመዳረሻዎች ዝርዝር መረጃ የያዘ መፅሐፍ ተዘጋጅቷል። በትግራይ ክልል ብቸኛ የሆነው ‘’የሐሸንገ ሐይቅ’’፣ የሕጉምብርዳ ተፈጥራዊ ደን፣ ለእይታ ማራኪ የሆነውን ጠመዝማዛው የግራት ካህሱ መንገድ ለመስህብነት ከተለዩ ስፍራዎች መካከል ይጠቀሳሉ ። ከባህር ጠለል በላይ 3ሺህ900 ሜትር ከፍታ ያለው የፅበት ተራራን ጨምሮ የአላጀ፣ፀርቀባ ተራሮችና በኢትዮጵያ የክርስትና ሀይማኖት እንዲስፋፋ ካደረጉ ተስዓቱ ቅድሳን ጥንታዊ የአባ ጉባ ቤተክርስትያን ዩኒቨርስቲው በጥናት ከለያቸው የመስህብ ስፍራዎች ውስጥ የሚካተቱ ናቸው ። የራያ ህዝብ ባህላዊ ጭፈራዎች፣ አለባበስና ኣመጋገብን ጨምሮ በዞኑ የሚገኙ ሀብቶች ለቱሪዝም አገልግሎት ለማዋል ዩኒቨርሲቲው እየሰራ መሆኑን ገልፇል ። የራያ ዩኒቨርሲቲ መምህርና የቱሪዝም ዘርፍ ተመራማሪ አቶ ኪሮስ ፀጋይ በዞኑ ከዚህ በፊት የማይታወቁና ለመድሃኒት ቅመማ ሊያገለግሉ የሚችሉ በርካታ እፅዋትን መኖራቸውን ገልፀዋል። እፅዋቶቹ ሳይንሳዊ መጠሪያ ተሰጥቶአቸው ጥቅም ላይ እንዲውሉ ዩኒቨርሲቲው ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑን አስረድተዋል ። በዩኒቨርስቲው የተጠኑ ጥናቶች እስከ 2013 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ ወደ ተግባር ለመቀየር እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የብቃት ማረጋገጫ ዳሬክቶሬት ዳሬክተር አቶ የማነ ገድሉ ናቸው። ቢሮው በክልሉ ከሚገኙ አራት ዩኒቨርስቲዎች ጋር በመተባበርና ሌሎች በውጭ የሚገኙ ምሁራኖችን በመጋበዝ የቱሪዝም ሀብቶችን ወደ ጥቅም ለመቀየር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።