እርምጃው ሰላማዊ የመማር ማስተማር ስራውን ለማስቀጠል ይረዳል...የዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶች - ኢዜአ አማርኛ
እርምጃው ሰላማዊ የመማር ማስተማር ስራውን ለማስቀጠል ይረዳል...የዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶች
ሆሳዕና፤ ጥር 20/ 2012 ዓ.ም (ኢዜአ) በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እየተወሰደ የሚገኘዉ እርምጃ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ስራን ለማስቀጠል የሚኖረዉ አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን የሶስት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንቶች ገለጹ። የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ዳምጠው ዳርዛ ለኢዜአ እንደገለፁት በሀገሪቱ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አንዳንድ ተማሪዎችና አመራሮች የትምህርት ተቋማትን ከተልዕኮ ዉጪ ለማራመድ በመሞከር ለሰላም እጦት ምክንያት እየሆኑ መጥተዋል።
የትምህርት ተቋማት የተለያዩ አካላትን የፖለቲካ አጀንዳ የሚንጸባረቅባችው መድረኮች እንዲሆኑ አንዳንድ ተማሪዎች ፣ መምህራንና ሰራተኞች ተገቢ ባልሆነ መንገድ ሲንቀሳቀሱ የሚስተዋልባቸው አጋጣሚዎች መስተዋላቸውን ተናግረዋል ።
መረጃን መሰረት ባደረገ መልኩ በጥፋት የተሳተፉ አካላት ላይ እየተወሰደ የሚገኘው እርምጃ ተገቢ በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አንስተዋል፡፡
እርምጃ በመወሰዱ የሰላም እጦት ይስተዋልባቸው የነበሩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ወደ ተረጋጋ የመማር ማስተማር ስራቸው መመለሳቸውንና ለሌሎች የትምህርት ተቋማትም ማስተማሪያ መሆኑናቸውን ዶክተር ዳምጠዉ ገልጸዋል፡፡
የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሀብታሙ አበበ በበኩላቸው የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚኒስቴር በዝግጅት ምዕራፍ የመማር ማስተማር ስራውን ውጤታማና ሰላማዊ ለማድረግ የሚከሰቱ ችግሮችን በውይይትና በምክክር እንዲፈታ ማድረግ አለበት።
ከዚያ ባለፈ በእኩይ ተግባር የሚሳተፉ አካላትን በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑ ለማድረግ አቅጣጫ በማስቀመጥ ተግባራዊ መደረጉ የተረጋጋ ሁኔታ እንዲመጣ ማስቻሉን ገልጸዋል።
ልዩነትን ማስኬድ የግለሰብ መብት መሆኑን የጠቆሙት ዶክተር ሀብታሙ ሀገሩን የሚወድ ዜጋ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ልዩነቱን በማራመድ ሀገር ተረካቢ ትውልድ ኮትኩቶ የማሳደግ ሃላፊነቱን በብቃት መወጣት እንዳለበት ጠቁመዋል ።
በዩኒቨርስቲዎች ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደትን ያወኩ አካላትን በመለየት ለህግ ቀርበው ተጠያቂ እንዲሆኑ ማድረግ ለሚስተዋሉ ችግሮች መፍትሄ እየሰጡ ከመምጣት ባሻገር ሰላማዊ የመማር ማስተማር ስራን ለማከናወን መሰረት ነው ብለዋል፡፡
መረጃን መሰረት ባደረገ መልኩ ህግን ማስከበር ተገቢ በመሆኑ አጥፊዎች ከድርጊታቸው እንዲማሩ መደረግ እንዳለበትም ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል፡፡
የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ፋሪስ ደሊል በበኩላቸው በዩኒቨርሲቲዎች አካባቢ የሚፈጠሩ አለመግባባቶች በህይወትና ንብረት ብሎም በጊዜ መባከን ከፍተኛ ዋጋን እያስከፈለ ነው ብለዋል፡፡
ከስሜታዊነት የጸዳ የአሰራር ስርዓትን የተከተለ እርምጃ መወሰድ እንዳለበትና የመማር ማስተማር ስራውን ወደ ነበረበት የሚመልስ አሰራር መዘርጋት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡
ሁሉም ተልዕኮውን እንዲወጣ ዓላማውን እንዳይስት የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባም ዶክተር ፋሪስ አሳስበዋል፡፡
በአርባምንጭ፣ ዋቸሞና ሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲዎች በተያዘው ዓመት የተከሰተ የጸጥታ ችግር አለመኖሩንና ይህን በማስቀጠል ተቋማቱ ከተሰጣቸው የመማር ማስተማርና የምርምር ስራ ባለፈ ከማህበረሰቡ ጋር በመቀናጀት ሁከት እንዳይከሰት የመከላከል ስራ እየተከናወነ መሆኑን ሶስቱም ፕሬዚዳንቶች ተናግረዋል።