ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ውሹ ሻምፒዮና ከሰኔ 24 ቀን ጀምሮ በአዳማ ከተማ ይካሄዳል

አዲስ አበባ ሰኔ 19/2010 ከማርሻል አርት ስፖርቶች መካከል አንዱ የሆነው ውሹ የ2010 ዓ.ም የኢትዮጵያ ሻምፒዮና ከሰኔ 24 እስከ 30 ቀን 2010 ዓ.ም ድረስ በአዳማ ከተማ የቀድሞ ምክር ቤት አዳራሽ ይካሄዳል። በሻምፒዮናው ላይ ከዘጠኙ ክልሎችና ሁለቱ ከተማ አስተዳድሮች የተውጣጡ ከ250 እስከ 300 ተወዳዳሪዎች ይሳተፉበታል ተብሎ ይጠበቃል። የኢትዮጵያ ውሹ ፌዴሬሽን የጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዳንኤል ዳኜ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የስፖርት ልዑካን ቡድን አባላት እርስ በርስ በማቀራረብ የወዳጅነት መንፈስ እንዲኖርና እንዲፈጠር ማስቻል የውድድሩ አላማ ነው። ሻምፒዮናው ተወዳዳሪዎች የስልጠና ውጤታቸውን በውድድሩ የሚመዝኑበትን መድረክ ከመፍጠር አንጻር ምቹ አጋጣሚ እንደሚፈጥር ገልጸዋል። ልዩ ተሰጥኦና ብቃት ያላቸውን ተወዳዳሪዎች ለብሔራዊ ቡድን በመመልመል በአህጉር አቀፍና ዓለም አቀፍ ደረጃ አገርን ወክለው በስፖርቱ እንዲሳተፉ ለማድረግ እንደሚያግዝም ተናግረዋል። በተጨማሪም ሻምፒዮናው የውሹ ስፖርት በክልሎችና በከተማ አስተዳድሮች ውስጥ ያለበትን ደረጃ ለማወቅና ለቀጣይ ስራዎች አቅጣጫ ለማስቀመጥ እንደሚረዳም ነው አቶ ዳንኤል ያስረዱት። ሻምፒዮናው በውሹ አርት ( በመሳሪያ እና ያለመሳሪያ ) እንዲሁም በነጻ ፍልሚያ (ከ48 እስከ 70 ኪሎ ግራም ዘርፍ) ተከፍሎ በሁለቱም ጾታ እንደሚካሄድ ጠቅሰዋል። የውሹ ስፖርት ራስን ከጥቃት ለመከላከል ከሚያበረክተው አስተዋፅኦ ባሻገር በአካሉ የዳበረ ጤናማ ዜጋ ለማፍራት ያለው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን አመልክተዋል። የውሹ ስፖርት እንደ ሌሎቹ የአርት ስፖርቶች ሁሉ መነሻው ከቻይና እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ። ውሹ የሚለው ቃል የመጣው ከቻይና  ሲሆን "ው" ማለት ወታደራዊ "ሹ" ደግሞ አርት ማለት ነው። ውሹ ከሌሎቹ የማርሻል ስፖርቶች የሚለየው እጅና እግርን እኩል በማስተባበርና የተለያዩ መሣሪያዎችን በመጠቀም የሚካሄድና የተመልካችን ቀልብ መያዝ የሚችል የስፖርት ዓይነት በመሆኑ እንደሆነ ይነገርለታል። የውሹ ስፖርት ወደ ኢትዮጵያ በዚህ ጊዜ ወይንም እንዲሁም በሌላ አገር ሰው ወደ አገሪቷ መጥቶ ተጀመረ ብሎ ለመናገር የሚያስችል የተደራጀ ሰነድ ባይኖርም በስፖርቱ እውቀትና ችሎታው ያላቸው ግለሰቦች በተለያዩ መጠሪያ የውሹ ስፖርትን በኢትዮጵያ አቆጣጠር በ1960ዎቹ ያዘወትሩትና ይለማመዱት እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም