ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ቻይናዊያን ቱሪስቶችን ለመሳብ ሁለት መንገዶችን ትከተላለች

ጥር 19 ቀን 2012 ( ኤዜአ) ኢትዮጵያ ከአገረ ቻይና በርከት ያሉ ቱሪስቶችን ለመሳብ እንደ ባሕላቸው ማስተናገድንና መስህቦቿን የማስተዋወቅ ስራዎች ለመስራት መዘጋጀቷን የባሕልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ገለጸ። መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በዓመት ከ200 ሚሊዮን በላይ ቻይናዊያን የተለያዩ የዓለም አገራትን ይጎበኛሉ። ከነዚህ በርካታ ቁጥር ካላቸው ጎብኚዎች መካከል 18 ቅርሶችን ለዓለም ያስተዋወቀችውን ኢትዮጵያን የሚጎበኟት ከ50  ሺህ የማይበልጡ ቻይናዊያን ናቸው። የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ዶክተር ሒሩት ካሳው መነሻቸውን ከቻይና ያደረጉ በርካታ ቱሪስቶችን ለመሳብና የቆይታ ጊዜያቸውን ለማራዘም 'ዘዴ ተቀይሷል' ይላሉ። ከእነዚህ መካከል ዋነኛው የቻይናዊያንን ባህል መሰረት ያደረጉ የመስተንግዶ፣ የምግብ አዘገጃጀትና አቀራረብ በክልሎች ጭምር ማስፋፋት ነው። ይህ ሁኔታ ቻይናዊያኑ ከአገራቸውና ባሕላቸው የራቁ ሳይመስላቸው የኢትዮጵያን ተፈጥሯዊ፣ ታሪካዊና ሃይማኖታዊ መስህቦች እንዲጎበኙ ያስችላል። ይህ ሲባል ግን የትኛውም የመስተንግዶ ሁኔታ የኢትዮጵያን ባሕልና እሴት በማይጻረር መልኩ የሚከናወን መሆኑ ሊታወቅ ይገባል ብለዋል ሚኒስትሯ። የኢትዮጵያዊንን ባህል፣ ማንነትና ስነልቦናዊ ሁኔታ ያላገናዘቡ የቱሪስት መሳቢያ መንገዶችም ሆኑ መስተንግዶዎች የሕግ ተጠያቂነትን እንደሚያስከትሉም ገልጸዋል። ሁለተኛው የቱሪስቶች መሳቢያ መንግድ በኢትዮጵያና በቻይና መካከል ዘመናትን ያስቆጠረውን ዲፕሎማሲ ተጠቅሞ ዘርፉን ማስተዋወቅ ነው እንደ ሚኒስትሯ ገለጻ። ይህ መንገድ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና በቻይና የኢትዮጵያ ኤምባሲ በኩል የሚከወን መሆኑን አክለዋል። ኢትዮጵያ በዘርፉ ካላት እምቅ አቅም አንጻር የቱሪስት መዳረሻዎችን የማስተዋወቅ ስራ እምብዛም አለመሰራቱንም አንስተዋል። በቀጣይ ሁሉንም አማራጮች በመከተል የማስተዋወቅና ገበያ የመፍጠር ስራ በስፋት እንደሚሰራ በመግለጽ። ከዚህ ጎን ለጎን ሚኒስቴር መስሪያ ቤታቸው የቱሪዝም መሰረተ ልማት የማስፋፋትና የማሻሻል ስራውን እንደሚያጠናክር ተናግረዋል። ምንም እንኳን የመሰረተ ልማት ማስፋፋት ስራ እየተሻሻለ ቢመጣም አሁንም ዘርፉ ጥራቱን የጠበቀ እንዲሆን ይደረጋል ነው ያሉት ዶክተር ሒሩት። ኢትዮጵያ ከውጭ አገራት ጎብኚዎች የውጭ ምንዛሬ እያገኘች ቢሆንም ሔድ መለስ የሚለው የሠላም እጦት ገቢው እንዲቀንስ እያደረገ መሆኑ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም