ቀጥታ፡

ለቶኪዮ 2020 ኦሎምፒክ ዝግጅትና ተሳትፎ አንድ ቢሊዮን ብር የመሰብሰብ ግብ ተቀምጧል

አዲስ አበባ፣ጥር 19/2020 (ኢዜአ) ለቶኪዮ ኦሎምፒክ ዝግጅትና ተሳትፎ አንድ ቢሊዮን ብር የመሰብሰብ ግብ መቀመጡን የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ገለጸ። ኮሚቴው ዛሬ የ'ቶኪዮ 2020 ኦሎፒክ' ዝግጅትን በተመለከተ የሚጠበቁ ተግባራትን አስመልክቶ ውይይት አካሂዷል። በዚሁ መሰረት ኮሚቴው የሚያከናውናቸው ዋና ዋና ተግባራት ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል። በውይይቱ እንደተገለጸው፤  ብሄራዊ የዝግጅት ኮሚቴ ማዋቀር፣ ገቢ ማሰባሰብ፣ ደጋፊ አባላት ማፍራት፣ ለአትሌቶች ሽኝት ማድረግና በውድድሩ የኢትዮጵያን ገጽታ ለመገንባት የሚያስችሉ ሁኔታዎችን ለመፍጠር የሚያስችሉ ተግባራትን ለማከናወን ዕቅድ ተይዟል። ኮሚቴው ደጋፊ አባላትን በማፍራት ለኦሎምፒክ ውድድሩ ዝግጅትና ተሳትፎ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ የማሰባሰብ ዕቅድ መያዙን የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስ ተናግረዋል። ገቢውን ለማሰባሰብ የታቀደው ከመንግስት፣ ከክልል ከተማ አስተዳደሮች ዝግጅትና ተሳትፎ፣ ከቴሌቶን የገቢ ማሰባሰቢያ ኘሮግራም፣ በአጭር የስልክ መልዕክት፣ ከስፖንሰር አድራጊዎች እንዲሁም ከኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ተቀማጭ እንደሆነ ተጠቁሟል። እንደ ዶክተር አሸብር ገለጻ፤ 12 ነጥብ 5 ሚሊዮን ደጋፊ አባላትን ለማፍራት ታስቧል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም