ቀጥታ፡

በ11ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ኢትዮጵያ ቡና ከቅዱስ ጊዮርጊስ ይገናኛሉ

በአዲስ አበባ ጥር 19 ቀን 2012 ( ኤዜአ)  በ11ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በሸገር ደርቢ ኢትዮጵያ ቡና ከቅዱስ ጊዮርጊስ የሚያገናኘው ጨዋታ ይጠበቃል። የሊጉ 11ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ነገ ረቡዕ ጥር 20 ቀን 2012 ዓ.ም በአዲስ አበባ እና በክልል ስታዲየሞች ይካሄዳሉ። በዚህም በተለይ በሸገር ደርቢ ኢትዮጵያ ቡና ከቅዱስ ጊዮርጊስ የሚያደርጉት ጨዋታ በስፖርት ቤተሰቦች ዘንድ የሚጠበቅ ሆኗል። በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ የበርካታ ደጋፊዎች ባለቤት የሆኑት ሁለቱ ክለቦች ደጋፊዎቻቸው በስፖርት ሜዳ ላይ በሚያሳዩዋቸው ማራኪ አደጋገፍና ህብረ ዝማሬ ይታወቃሉ። ከዚህ ቀደም ሁለቱ ክለቦች በሚገናኙበት ጨዋታዎች ላይ ጨዋታውን ለመከታተል በርካታ ደጋፊዎች በስታዲየም ይታደማሉ። ይሁንና በዚህ አመት ሁለቱ ክለቦች ባደረጉት የስታዲየም መግቢያ ማሻሻያ ምክንያት በርካታ ደጋፊዎች ቅሬታቸውን ሲያነሱና በርካቶችም ከሜዳ ርቀው ተስተውሏል። ከ30 እስከ 35 ሺህ ተመልካቾችን እንደሚይዝ የሚነገርለት የአዲስ አበባ ስታዲየም ነገ ታላቁን የሸገር ደርቢ ሲያስተናግድ እንደ ወትሮው በየክለቦቹ ደጋፊዎች ይደምቃል ተብሎ ይጠበቃል። ጨዋታው ነገ ከቀኑ በ10:00 ሰዓት በአዲስ አበባ ስታዲየም የሚደረግ ይሆናል። ሁለቱ ክለቦች በሸገር ደርቢ እርስ በርስ በተገናኙባቸው ጨዋታዎች ቅዱስ ጊዮርጊስ 20 ጊዜ ሲያሸንፍ ኢትዮጵያ ቡና የ7 ጊዜ ድል አስመዝግቧል፤ 13 ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። በሌሎች የሊጉ 11ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ድሬደዋ ከተማ ከሰበታ ከተማ፣ ሀዲያ ሆሳዕና ከወልቂጤ ከተማ፣ ጅማ አባጅፋር ከፋሲል ከነማ፣ ሀዋሳ ከተማ ከወላይታ ዲቻ፣ ባህርዳር ከተማ ከአዳማ ከተማ እንዲሁም መቀለ ሰብአ እንደርታ ከስሁል ሽረ ነገ በተመሳሳይ 9:00 ሰዓት ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። ሲዳማ ቡና ከወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ደግሞ ሐሙስ 9:00 ሰዓት ጨዋታቸውን የሚያደርጉ ይሆናሉ። የደረጃ ሰንጠረዡን መቀለ ሰብአ እንደርታ በ19 ነጥብ ሲመራ ፋሲል ከነማ በ18 እንዱሁም ቅዱስ ጊዮርጊስ በ17 ነጥብ ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።   ወልቂጤ ከተማ፣ ድሬዳዋ ከተማና ሀዲያ ሆሳዕና ከ14 እስከ 16ኛ ደረጃ ላይ በመሆን የሊጉ ግርጌ ላይ ይገኛሉ።                  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም