የምርምር ማዕከሉ ከፍተኛ ምርት የሚሰጡ 11 ዓይነት የማሽላ ዝሪያዎችን ለአርሶ አደሩ እያስተዋወቀ ነው

54
ሁመራ፣ ጥር 19/2012 (ኢዜአ) የሁመራ ግብርና ምርምር ማዕከል ድርቅና በሽታን ተቋቁመው ከፍተኛ ምርት የሚሰጡ 11 ዓይነት የማሽላ ዝሪያዎችን ለአርሶ አደሩ እያስተዋወቀ መሆኑን ገለጸ። ማዕከሉ እያስተዋወቃቸው ካሉት ዝሪያዎች መካከል ደቂባ፣ተሻለ፣ መልካም፣አብሽር እና ኢ. ሴ. ኤች አንድ የተባሉ ይገኙበታል። በትግራይ ምዕራባዊ ዞን ለሚገኙ አርሶ አደሮች በማስተዋወቅ ማዕከሉ እያላመዳቸው ያሉት የማሽላ ዝሪያዎቹ ከነባሮቹ በሄክታር ከሁለት እጥፍ በላይ  ምርት የሚሰጡ ናቸው። የምርምር ማዕከሉ አስተባባሪ አቶ ገብረኪሮስ ማሩ እንዳሉት  የአካባቢው ነባር የማሽላ ዝርያዎች  እስከ 20 ኩንታል ሲሰጡ በማስተዋወቅ ላይ ያሉት እስከ 45 ኩንታል በሄክታር ምርት እንደሚሰጡ በምርምር ተረጋግጧል። በሽታንና ድርቅን ተቋቁመው በሦስት ወራት ውስጥ ለፍሬ እንደሚደርሱ  ገልጸው ነባሮቹ ግን ከስድስት ወራት በላይ እንደሚወስድባቸውና በበሽታም የሚጠቁ መሆናቸውን አስረድተዋል። ዝሪያዎቹን ለተመረጡ የዞኑ አርሶ አደሮች በቂ ስልጠና በመስጠት በማሳቸው ላይ አስፋፍተው እንዲያለሙ እየተደረገ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ በማዕከሉ የማሽላ አዝርዕት ተማራማሪ አቶ ገብረ መድህን ገብረ ጊዮርጊስ  ናቸው። እንደ ተመራማሪው ገለፃ ፣ ምርታማ የሆኑት የማሽላ ዝሪያዎቹ ለእንጀራ ጨምሮ ለተለያዩ የምግብ ዓይነቶች የሚውሉ ናቸው። በተለይ ደቂባ እና መልካም የተባሉ የማሽላ ዝርያዎች የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ የተለያዩ በሽታዎችን የመከላከል አቅም ያላቸው ንጥረ ነገር የያዙና ፈጥነው ለፍሬ የሚደርሱ  እንደሆኑ  አስረድተዋል። በዞኑ ቃፍታ ሁመራ ወረዳ የራዊያን ቀበሌ አርሶ አደር ማውጫ ገብረስላሴ በሰጡት አስተያየት  በአከባቢያቸው የነበሩ የማሽላ ዝርያዎች  ብዙም ምርት እንደማይሰጡ ተናግረዋል። የምርምር ማዕከሉ ያስተዋወቃቸው የ"ደቂባ" ዝሪያ በማሳቸው ላይ በማላመድ እያመረቱ በመሆኑ  የተሻለ ምርት እንደሚጠብቁ ገልጸዋል።                            
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም