ቀጥታ፡

በስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ ለፀረ-አበረታች ቅመሞች ምርምራ የ186 ስፖርተኞች የደምና ሽንት ናሙና ኳታርና ኬንያ ተልኳል

አዲስ አበባ ጥር 18/2012 (ኢዜኣ) የበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ስድስት ወራት የ186 ስፖርተኞች የደምና ሽንት ናሙና ተሰብስቦ ለምርምራ ኳታርና ኬንያ መላኩን የኢትዮጵያ ብሔራዊ የፀረ-አበረታች ቅመሞች ጽህፈት ቤት አስታወቀ። አበረታች ቅመሞችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር እየተከናወነ ባለው ስራ ተጫባጭ ውጤቶች መመዝገባቸውን ገልጿል። የጽህፈት ቤቱ የምርመራና ውጤት አስተዳደር ዳይሬክተር ተስፋዬ ይፍሩ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ የስፖርተኞችን የሽንትና ደም ናሙና በየዓመቱ ዓለም አቀፉ የፀረ- አበረታች ቅመሞች ጽህፈት ቤት (ዋዳ) ፈቃድ በሰጣቸው ዓለም አቀፍ የምርመራ ቤተ ሙከራዎች ታስመረምራለች። በመሆኑም በስድስት ወራት ውስጥ በአትሌቲክስ የ117፣ ቦክስ የ26፣ ክብደት ማንሳት የ11፣ ወርልድ ቴኳንዶና በብስክሌት በተመሳሳይ ዘጠኝ፣ በፓራ ኦሊምፒክ ስምንትና በእግር ኳስ ስድስት ስፖርተኞች በድምሩ የ186 ስፖርተኞች ናሙና ወደ ኳታርና ኬንያ መላኩን ተናግረዋል። የውሃ ዋና ስፖርት በጽህፈት ቤቱ የአበረታች ምርመራ ቋት ውስጥ እንደሚገኝና በቀጣይ ወቅቱን ጠብቆ በስፖርቱ ባሉ ተወዳዳሪዎች ላይ የሽንት የደም ናሙና ተሰብስቦ ለምርምራ እንደሚላክ ጠቁመዋል። ናሙና የመላክ ተግባሩ እንደሚቀጥል የገለጹት አቶ ተስፋዬ፤ የደም ምርመራ በኬንያ ለሚገኝ የአበረታች ቅመሞች ምርምራ ቤተ ሙከራ እንዲሁም የሽንት ምርመራ ኳታር ለሚገኝ ቤተ ሙከራ መላኩን አመልክተዋል። በሁለቱ አገሮች የሚደረገው ምርመራ የተለያዩ ሳይንሳዊና ቴክኒካዊ ሂደቶችን የሚያልፍ በመሆኑ ውጤቱ የሚታወቅበት ጊዜ እንደማይታወቅ ገልጸዋል። ከስፖርተኞች ናሙና የሚወሰደው በውድድር ወቅትና ከውድድር ውጪ ሲሆን ድንገተኛና ሚስጥራዊ በሆነ መንገድ የሚከናወን ተግባር እንደሆነ ተናግረዋል። ዋዳ ከሁለት ዓመት በፊት የአበረታች ቅመም ችግር ከሚስተዋልባቸው አምስት አገሮች አንዷ ኢትዮጵያ መሆኗን፣ ችግሩን ለመፍታትም በቂ ቁርጠኝነት እንዳላሳየችና ችግሩን ለመፍታት የሚያስችል ተቋም እንድትመሰርት ትዕዛዝ ሰጥቷት እንደነበር አቶ ተስፋዬ አስታውሰዋል። በወቅቱ በኢትዮጵያ አበረታች ቅመሞች በመድሐኒት ቤቶች እንደሚሸጡና አበረታች ቅመም የሚወስዱ አትሌቶች እንዳሉ የሚገልጽ ዘገባ በመገናኛ ብዙሃን በመውጣቱ ኢትዮጵያ ስጋት ውስጥ ገብታ እንደነበር ገልጸዋል። በመንግስት ድጋፍ ኢትዮጵያ ችግሩን ለመፍታት ጽህፈት ቤት አቋቁማ እየሰራች እንደምትገኝ ገልጸው፤ አበረታች ቅመም ወስደው በተገኙ አትሌቶች ላይ እገዳ መጣሉንና ዘጠኙ መቀጣታቸውን ተናግረዋል። አበረታች ቅመም በሸጡት ግሸንና በዮሐና ፋርማሲዎች ላይ ህጋዊ እርምጃ መወሰዱንም አስታውሰዋል። ስፖርተኞች ስለ አበረታች ቅመም ያላቸው ግንዛቤ እያደገ በመምጣቱ ለምርመራ ፈቃደኝነታቸው መጨመሩን የተናገሩት አቶ ተስፋዬ፤ ስፖርተኞቹ የመከላከል እንቅስቃሴውን መደገፍ መጀመራቸውንም አመልክተዋል። ኢትዮጵያ ባለፈው በጀት ዓመት ኢትዮጵያ የ664 ስፖርተኞችን የሽንትና የደም ናሙና ሰብስባ ለምርምራ መላኳን ከኢትዮጵያ ብሔራዊ የፀረ-አበረታች ቅመሞች ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።            
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም