ነባር የስኳር ፋብሪካዎች በሙሉ አቅማቸው እንዲያመርቱ በመደረጉ ውጤታማ እየሆኑ ነው

84
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 18/2012  ነባር የስኳር ፋብሪካዎች በሙሉ አቅማቸው እንዲያመርቱ በማድረግ ረገድ በአንድ ዓመት ውስጥ ውጤት እየታየ መሆኑን የስኳር ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ወዩ ሮባ ገለጹ። ዋና ስራ አስፈጻሚው ለኢዜአ እንደገለጹት ፋብሪካዎቹ ቀደም ሲል በተቀመጠላቸው መጠንና ጥራት ልክ እያመረቱ አልነበረም። የአደረጃጀት ችግር፣ ቋሚ የጥገናና የስራ ጊዜ ተለይቶ አለመተግበርና ሌሎችም ችግሮችን በምክንያትነት ጠቅሰዋል። ፋብሪካዎቹ ስራ ከጀመሩ በኋላ ለጥገና ስለሚቆሙና ለዚህም የማካካሻ አሰራር ስላልነበራቸው ከታቀደላቸው የምርት መጠን በአማካይ በግማሽ ሲያመርቱ ቆይተዋል። ባለፈው በጀት ዓመት በነባር ፋብሪካዎች አሰራር ላይ በተደረገው ለውጥ ችግሮቹ በመቃለላቸው የምርት መጠናቸው በዕጥፍ እየጨመረ መሆኑን ተናግረዋል። ዘርፉ ውጤታማ ሳይሆን የቆየበትን ምክንያት ሲገልጹም ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ዘርፉ የሚጠይቀውን የሰው ኃይል ማግኘት ባለመቻሉ እንደነበር ተናግረዋል። አሁን ግን ለስኳር ዘርፍ በቀጥታ ተግባር ላይ የሚውሉ የትምህርት ሙያዎችን በመለየት ካሪኩለም እንዲቀረፅና ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ ጋር በመዋዋል እስከ ሁለተኛ ዲግሪ ድረስ የተማሩና ክህሎት ያላቸው ባለሙያዎች ማፍራት ተጀምሯል ብለዋል። ፋብሪካዎቹ ወደ ሙሉ የማምረት አቅም እንዲመጡ ከማድረግ ጋር ተያይዞ የሚካሄዱ ጥገናዎችን ተከትሎ በርካታ ገንዘብ ለውጭ ባለሙያዎች ይወጣ እንደነበር የጠቀሱት አቶ ወዩ በአገር ውስጥ ባለሙያዎች ጥገና በማካሄድ በርካታ ገንዘብ ከወጪ ማዳን ተችሏል ብለዋል። ለአብነት የፊንጫ ስኳር ፋብሪካን የጠቀሱ ሲሆን በሌሎች ነባር ፋብሪካዎችም ተመሳሳይ ለውጥ እየመጣ መሆኑን አክለዋል። በቀጣዮቹ ሶስት ዓመታትም ፋብሪካዎቹ በሙሉ አቅማቸው የሚጠበቅባቸውን የምርት መጠንና ጥራት አሟልተው እንዲያመርቱ ማድረግ ይቻላል ነው ያሉት።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም