ቀጥታ፡

የመንግስትና የግል ተቋማት አመራርና ሠራተኞች በቦንብ ጥቃቱ የተጎዱ ዜጎችን እየጎበኙ ነው

አዲስ አበባ ሰኔ 18/2010 የመንግስትና የግል ተቋማት አመራርና ሠራተኞች በቦንብ ጥቃቱ የተጎዱ ዜጎችን እየጎበኙ ነው። የፌዴሬሽን ምክር ቤት፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት እንዲሁም የኢትዮጵያ ባዮ ጋዝ ኢንስቲትዩት አመራርና ሠራተኞች በመስቀል አደባባይ በደረሰው ፍንዳታ የተጎዱ ዜጎችን በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ተገኝተው ጎበኙ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አሕመድ በአጭር ጊዜ ውስጥ ላስመዘገቡት ለውጥ ድጋፍና ዕውቅና ለመስጠት ከትናንት በስቲያ ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም በመስቀል አደባባይ በተጠራው ሰልፍ ላይ የቦንብ ጥቃት መከሰቱ ይታወሳል። የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሂም፣ የአዲስ አበባ ዩኒሸርሲቲ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና፣ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ኢንጅነር መላኩ እዘዘው እንደዚሁም የኢትዮጵያ ባዮ ጋዝ ኢንስቲትዩት አመራርና ሠራተኞች በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ተገኝተው በጥቃቱ የተጎዱ ዜጎችን ጎብኝተዋል። በዚሁ ወቅትም ጥቃቱ በሁሉም የኢትዮጵያ ህዝቦች ላይ የተሰነዘረ የሽብር ድርጊት መሆኑን በመጠቆም ተግባሩን ያወገዙ ሲሆን በጥቃቱ ህይወታቸውን ላጡና ለተጎዱ ዜጎች የተሰማቸውን ሃዘን ገልፀዋል። በደረሰው ጥቃት የተጎዱ ዜጎችን አበረታተዋል፤ ከጎናቸው እንደሚቆሙም ቃል ገብታዋል። በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የነርሲንግ ዳይሬክተር ነርስ ሳራ ካህሳይ እንደገለፁት፤ በሆስፒታሉ የህክምና እርዳታ ሲደረግላቸው ከቆዩ 86 ተጎጂዎች ውስጥ 14ቱ የጽኑ ህሙማን ክፍል ውስጥ ገብተው 2ቱ ህይወታቸው ቢያልፍም 12ቱ የህክምና እርዳታ እየተሰጣቸው እንደሚገኙና በጥሩ ጤንነት ውስጥ እንዳሉ ገልፀዋል። በደረሰው ፍንዳታ ጉዳት ከደረሰባቸው ዜጎች መካከል ወይዘሮ እታፈራው ውብሸት፤ በሰጡት አስተያየት በተፈፀመው ጥቃት የደረሰባቸውን ጉዳት "ለሀገሬ መስዋእት እንደከፈልኩ አድርጌ ነው የምቆጥረው፤ አሁንም ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጎን ለመሰለፍ ዝግጁ ነኝ" ብለዋል። የአደጋው ሰለባዎች በተለያዩ ሆስፒታሎች ህክምና እየተደረገላቸው ሲሆን በዕለቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩና ሌሎች ከፍተኛ ባለስልጣናት በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በመገኘት ጎብኝተዋቸዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም