የስጋ ደዌ በሽታን ለመከላከልም ሆነ ተጠቂዎችን ለመደገፍ ስለበሽታው ዕውቀት ያስፈልጋል

189
አዲስ አበባ ጥር 17 ቀን 2012  (ኢዜአ ) የስጋ ደዌ በሽታን በህክምናው ለመከላከልም ሆነ ተጠቂዎችን ለመደገፍ እንዲሁም ሁለንተናዊ መብታቸውን ለማስጠበቅ በቅድሚያ ስለበሽታው ማወቅ እንዳለባቸው ተገለጸ። በዓለም ለ66ኛ በአገራችን ደግሞ ለ21ኛ ጊዜ የሚከበረውን አለም አቀፍ የስጋ ደዌ ቀንን ምክንያት በማድረግ የኢትዮጵያ ብሔራዊ የስጋ ደዌ ተጠቂዎች ማህበር በበሽታው ምንነት ላይ ውይይት አካሂዷል። "በዕውቀትና በፍቅር የተመሠረተ ሁለንተናዊ አገልግሎት በመስጠት ከስጋ ደዌ ነጻ የሆነ ማህበረሰብ እንፍጠር"  በሚል መሪ ሐሳብ ስለበሽታው፣ ስለ ተጠቂዎች የህክምና አገልግሎት እንዲሁም ስለ ህጋዊ ስምምነቶችና ተፈጻሚነታቸው ላይ ያተኮረ ውይይት ነው። በዚህም በግንዛቤው በህክምና አሰጣጥ፣ ለተጠቂዎቹ ስለሚደረግ ድጋፍና አገራዊ ተደራሽነት እንዲሁም የተጠቂዎቹን መብት ማስጠበቂያ አለም አቀፋዊ ስምምነቶች አስገዳጅ ያለመሆናቸው ተጠቁሟል። ከማህበሩ የተገኙ መረጃዎች እንዳሳዩት በሽታው በየዓመቱ ከ3 እስከ 4 ሺህ ዜጎቻችንን እንደሚያጠቃ እና ከእነዚህም ውስጥ 15 በመቶዎቹ ህጻናት መሆናቸው ተገልጿል። በአለርት ሆስፒታል የፕላስቲክና ሪኮንስተራክቲቭ ሰርጂን ዶክተር አትክልቲ ባራኪ በአገራችን ያለው ህክምና፣ በተጠቂዎችና እና በህብረተሰቡ ያለው የግንዛቤ ክፍተት “በበሽታው ላይ ያለ የህክምና ችግር” ነው ብለዋል። ቢሆንም ህክምናውን አካላዊ ጉዳት ካደረሰ በኋላ ስለሚጀምሩ ወደ ቀድሞ ህይወትና የአካል ብቃት ስለማይመለሱ ለስነ ልቦናዊ፣ ለኢኮኖሚያዊና ለማህበራዊ ችግሮች ይጋለጣሉ ብለዋል። ከዚህም የተነሳ ራሳቸውንም ከማህበረሰቡ ያገላሉ፤ ህብረተሰቡም ባለው ዝቅተኛ አመለካከት የተነሳ ያገላቸዋል ይላሉ ዶክተር አትክልቲ። እንደ ዶክተር አትክልቲ፤ ታካሚዎቹ በሽታው በሰውነታቸው ምልክት እንዳሳዬ ወዲያው ህክምና ቢጀምሩ ኖሮ በአካላቸው ላይ ጉዳት ሳይደርስ መዳን ይችላሉ። ስለሆነም ምልክት እንደታዬ ህክምናውን ሲጀምሩ በሽታው በተጠቂዎቹ ላይ ኢኮኖሚያዊ፣ ስነ-ልቦናዊ እና ማህበራዊ ችግርን ከማስከተሉ በፊት መፈወስ ይችላሉ ብለዋል። ታማሚዎቹ የስጋ ደዌን በሽታ ምልክቱ እንደታየ እስከመጀመሩ ድረስ ችግሩ ህክምናን የሚመለከት እንጂ ኢኮኖሚን፣ ማህበራዊንና ስነልቦናን የሚመለከት እንዳልሆነም አስረድተዋል። ዶክተር አትክልቲ ተጠቂዎቹ በሽታው በሚያስከትለው አካላዊ ለውጥና ጉዳት ራሳቸውና ከማህበረሰቡ ከሚያገልሉ እንደማንኛውም በሽታ እንደሚድን በማሰብ ወዲያው እንዲታከሙም መክረዋል። የህግ ባለሙያው አቶ ይልቃል ሀሳቤ ደግሞ ለስጋ ደዌ ተጠቂዎች ተሳታፊነትና ተጠያቂነትን ለማሳደግ ላይ የወጡ የህግ ማዕቀፎች አተገባበርና ተግዳሮቶች መኖራቸው ብቻ ሳይሆን ያሉትም ተፈጻሚነታቸው የላሉ መሆናቸውን ተናግረዋል። እንደ አቶ ይልቃል፤ አገራችን የስጋ ደዌ ተጠቂዎችን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መብቶቻቸውንና ተሳትፏቸውን ያረጋገግጠና እኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን የሚያሳድግ አገራዊ ማዕቀፍ የላትም። በበሽታው የከፋ የአካል ጉዳት የደረሰባቸውን ተጠቂዎችን ማገዝ የሚያስችል የህግና የፖሊሲ እንዲሁም ህገ-መንግስታዊ ድጋፍ እንደሌለም ጠቁመዋል። ይህም በመሆኑ አሁን ላይ የአካል ጉዳት ሰለባ ለሆኑ ተጠቂዎች የማገገሚያ ድጋፍ እየተደረገ ያለው በጥቅል በአካል ጉዳተኞች በወጣው ህግና ፖሊሲ መሆኑን ነው አቶ ይልቃል የሚናገሩት። አገሪቷ ከዚህ በፊት የተለያዩ አለም አቀፋዊ ስምምነቶችን ብትፈርምም በዘርፉ ያሉት አስገዳጅ ባለመሆናቸውም ተፈጻሚነት እንደሌላቸው ገልጸዋል። ስለሆነም አገራችን በስጋ ደዌ ተጠቂ አካል ጉዳተኞችን ጨምሮ 17 በመቶ የህዝብ ቁጥሯ አካል ጉዳተኞች በመሆናቸው መንግስት የሚያወጣቸው ማናቸውም ህጎችና ፖሊሲዎች የስጋ ደዌ ተጠቂዎችን ያማከሉና ያገናዘቡ እንዲሆኑ አሳስበዋል። የብሔራዊ ማህበሩ ስራ እስኪያጅ አቶ ተስፋየ ታደሰም ስለበሽታው አገራዊ ብቻ ሳይሆን አለም አቀፋዊ የህክምናና ግንዛባቤ ክፍተቶች አሉ ብለዋል። አቶ ተስፋዬ አክለውም የባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ መፍትሔ እንደሚያሻ አውስረድተዋል። የጤና ሚኒስቴርም ህክምናውንና ግንዛቤ ማስጨበጫውን ለሁሉም ተደራሽ ለማድረግ ምን እየሠራ ነው? በሚል ከተሳታፊዎቹ ለተነሳው ጥያቄም በከሚኒስቴሩ የበሽታዎች ቁጥጥርና ክትትል ዳይሬክተር ወይዘሮ ህይወት ሰለሞን ምላሽ ሰጥተዋል። ወይዘሮ ህይወት እንዳሉት ህክምና መስጫ መድሃኒቶች ላይ ችግር እንደሌለ ገልጸው ለግንዛቤ ክፍተቱ ግን የሁሉም አካላት ጥረት እንደሚያስፈልግ ጠቅሰዋል። አንዳንድ ጊዜ ለሚፈጠሩ የተደራሽነትና የህክምና አገልግሎት መስጫ ተቋማትን ያተኮረ የሰው አቅም ግንባታና የቁሳቁስ ማሟላት ስራ እየሰሩ መሆናቸውንም ገልጸዋል። ሚኒስቴሩ በይበልጥ ተጋላጭ የሆኑ 93 ወረዳዎችንና መካከለኛ ተጋላጭ 121 ወረዳዎችን ለይቶ በትኩረት እየሰራ መሆኑንም አስረድተዋል። የኢትዮጰያ የስጋ ደዌ ማህበር ከስጋ ደዌ በተጨማሪ ዝሆኔንም ለመከላከል ከዘርፉ ባለሙያዎች ጋር እየሰራ ሲሆን ለዚህም ወደፊት ስራውን የሚያግዝ ህንጻ በ34 ሚሊዮን ብር እያስገነባ ይገኛል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም