የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ አራተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ተካሄዱ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ አራተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ተካሄዱ
አዲስ አበባ ፤ጥር 16/2012 የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ አራተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ተካሂደዋል።
በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም ሦስት ጨዋታዎች ተደርገዋል።
ቂርቆስ ክፍለ ከተማ የፌዴራል ማረሚያ ቤቶችን 38 ለ24 በሆነ ውጤት ያሸነፈ ሲሆን ውጤቱን ተከትሎ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ነጥቡን ወደ 8 ከፍ በማድረግ የሊጉ መሪነቱን አጠናክሯል።
ፌዴራል ፖሊስ ቡታጅራ ከተማን 34 ለ19 በሆነ ውጤት አሸንፏል።
በአዲስ አበባ ትንሿ ስታዲየም በተደረገ የመጨረሻ ጨዋታ መከላከያ የአምናውን የሊጉ አሸናፊ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማን 29 ለ24 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል።
በተመሳሳይ በክልል ከተሞች ሁለት ጨዋታዎች የተደረጉ ሲሆን ቦንጋ ላይ መቐለ 70 እደርታ ሚዛን ከተማን 53 ለ26 በሆነ ውጤት ረትቷል።
ዱራሜ ላይ ከንባታ ዱራሜ ጎንደር ከተማን 32 ለ26 በሆነ ውጤት አሸንፏል።
የፕሪሚየር ሊጉን የደረጃ ሰንጠረዥ ቂርቆስ ክፍለ ከተማና መቐለ 70 እንደርታ በተመሳሳይ 8 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው አንደኛና ሁለተኛ ደረጃን ይዘዋል።
ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ በ6 ነጥብ ሦስተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠ ሲሆን ሚዛን አማን ከተማ ደግሞ ያለምንም ነጥብ አስረኛ ደረጃን ይዟል።