የኢትዮጵያ የመንገድ ደህንነት ማህበር ስራውን በይፋ ጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የመንገድ ደህንነት ማህበር ስራውን በይፋ ጀመረ
አዲስ አበባ፤ ጥር 16/2012 በመንገድ ደህንነት ላይ የሚሰራው በበጎ ፈቃደኛ ሰዎች የተመሰረተው የኢትዮጵያ የመንገድ ደህንነት ማህበር ዛሬ ስራውን በይፋ ጀመረ።
በኢትዮጵያ የትራፊክ አደጋ በሰው ህይወትና ንብረት ላይ እያደረሰ ያለው ጉዳት አስከፊ ደረጃ ላይ እየደረስ መጥቷል።
ጥናቶች እንደሚያመለክቱት በዓለም አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በትራፊክ አደጋ ህይወታቸውን ሲያጡ ከ50 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ደግሞ ለአካል ጉዳተኝነት ይዳረጋሉ።
ከ85 በመቶ በላይ የሚሆኑት አደጋዎች የሚከሰቱት በዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ባላቸው አገሮች ሲሆን እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ታዳጊ አገሮች ዕድገት ላይ የ2 በመቶ የኢኮኖሚ ኪሳራ እንደሚያጋጥም በጥናት ተረጋግጧል።
በኢትዮጵያ እየደረሰ ያለውን የትራፊክ አደጋ ለመቀነስ ዓላማ ያደረገ የኢትዮጵያ የመንገድ ደህንነት ማህበር ዛሬ በበጎ ፍቃደኞች ተመስርቷል።
ማህበሩ መንግስት የትራፊክ አደጋ እያስከተለ ያለውን ጉዳት ለመቀነስ በተለያዩ አደረጃጀቶች እያከናወነ ያለውን ስራ ለማገዝና ኅብረተሰቡ በትራፊክ አደጋ ላይ ግንዛቤ በማስጨበጥ የድርሻውን ለመወጣት እንደሚሰራም ገልጿል።
እንዲሁም የትራፊክ አደጋን በመከላከል ረገድ ኅብረተሰቡ በመንገድ አጠቃቀምና የትራፊክ መብራትን ጠብቆ መንገድ ማቋረጥ ላይ ግንዛቤ የመፍጠር ስራ ዓላማው እንደሆነም አስታውቋል።
በማህበሩ የምስረታ መርሐ ግብር ላይ የተገኙት የትራንስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሙሉ ገብረእግዚአብሔር በበኩላቸው የትራፊክ አደጋ ሁሉንም የኀብረተሰብ ክፍል የሚነካ በመሆኑ ሁሉንም ያሳተፈ የመከላከል ስራ መስራት እንደሚገባ ገልጸዋል።
በበጎ ፈቃደኞች የተመሰረተው ማህበር ይዞት የተነሳው ዓላማ ወቅቱን የጠበቀና አገራዊ ፋይዳው የጎላ በመሆኑ የማህበሩ ዓላማ ከግብ እንዲደርስ ሁሉም እንዲረባረብ ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ የመንገድ ደህንነት ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ዮናስ ወልደሰማያት በበኩላቸው የትራፊክ አደጋ የሁሉንም ቤት የሚያንኳኳ በመሆኑ ጊዜ ሊሰጠው የማይገባና ትኩረት የሚያሻው እንደሆነም ገልጸዋል።
ማህበሩ ከመንግስት በኩል የሚያስፈልገውን የምዝገባ ፈቃድ አሟልቶ 'የኢትዮጵያ የመንገድ ደህንነት ማህበር' በሚል ስያሜ ስራውን ዛሬ በይፋ ጀምሯል።
በኢትዮጵያ በትራፊክ አደጋ በየሁለት ሰዓቱ አንድ ሰው ለህልፈተ ህይወት እንደሚዳረግ በዘርፉ የተደረገ አንድ ጥናት ያመለክታል።
ጥናቱ እንዳመለከተው በቀን 13 ሰዎች በትራፊክ አደጋ ህይወታቸውን ያጣሉ።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ የትራፊክ አደጋ አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን ጥናቱ አረጋግጧል።