የዶሮን ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲቀርብ ለማስቻል በመኖ አቅርቦት ላይ ያለው ችግር እንዲፈታ ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
የዶሮን ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲቀርብ ለማስቻል በመኖ አቅርቦት ላይ ያለው ችግር እንዲፈታ ተጠየቀ
አዲስ አበባ፣ ጥር 16/2012 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ የዶሮ ስጋና እንቁላልን በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ የመኖ አቅርቦት ላይ የሚታየውን ችግር በቅድሚያ መፍታት እንደሚያስፈልግ የኢትዮጵያ ዶሮ አርቢዎችና አቀናባሪዎች ማህበር ገለፀ። ማህበሩ አመታዊ ጠቅላላ ጉባኤውን ዛሬ አዲስ አበባ ሲያካሂድ የማህበሩ ስራስኪያጅ ዶክተር ምስግና ፍፁምብርሃን እንዳሉት፤ የዶሮ ምርት ጠቃሚ የፕሮቲን ንጥረ ነገርን በመያዙ በእለት ተእለት ምግብ ውስጥ መካተት አለበት። የዶሮ ምርት በአብዛኛው አገልግሎት ላይ የሚውለው በበዓል ወቅት ብቻ መሆኑ ትክክል እንዳልሆነ ገልጸዋል። ህብረተሰቡ የዶሮ ምርትን ዘወትር መጠቀም እንዲችል በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ አሁን የሚታየው የመኖ ችግር እንዲፈታ መሰራት እንዳለበት ጠቁመዋል። መንግስት በመኖ አቅርቦት ስራ ለሚሰማሩ ባለሃብቶች ማበረታቻ በመስጠት መደገፍ እንዳለበትም አመልክተዋል። የዶሮ አምራቾች እንደሚሉት፤ ለምርቱ ከሚጠየቀው ገንዘብ ውስጥ 70 በመቶ የሚሆነው ለመኖ ግዥ ይውላል። የተበለቱ ዶሮዎችን ከውጭ አገር ለማስገባ የሚወጣውን የውጭ ምንዛሬ ምጣኔ ለመቀነስ የአገር ውስጥ አምራቾች በመንግስት መደገፍ እንዳለባቸው ተጠቁሟል። ማህበሩ በአገር ውስጥ የዶሮና እንቁላል ምርት ገበያ ላይ የደላሎች ጣልቃ ገብነት እንዳይኖርና አዲስ አሰራርን ለመተግበር እየተዘጋጀ መሆኑም ተገልጿል። በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ባለው ወቅታዊ ሁኔታና አለመረጋጋት በዘርፉ የተሰማሩ ኢንተርፕራይዞች ከስራ እንዲወጡ እያደረገ መሆኑንም አንስተዋል። ማህበሩ የአባላቱን አቅም ለማሳደግ የተለያዩ ስልጠናዎችን ያካሔደ ሲሆን ወደ ውጭ አገሮች አቅንተው የልምድ ልውውጥ እንዲያገኙም እያደረገ ነው ተብሏል። የኢትዮጵያ ዶሮ አርቢዎችና አቀናባሪዎች ማህበር በ2003 ዓ.ም የተመሰረተ ሲሆን 96 አባላት አሉት።