የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ለመንግስት ምስጋና አቀረበ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ለመንግስት ምስጋና አቀረበ
አዲስ አበባ፤ ጥር 16/2012(ኢዜአ) የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት መንግስት 'ለ60 ዓመታት ገደማ' ያቀረበውን ጥያቄ ለመመለስ ውሳኔ በማስተላለፉ መደሰቱን በመግለጽ ምስጋና አቅርቧል። የሚኒስትሮች ምክር ቤት ከትናንት በስቲያ ባካሄደው 78ኛ መደበኛ ስብሰባው በስድስት ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ ማሳለፉ ይታወቃል። ውሳኔ ካሳለፈባቸው አጀንዳዎች መካከል የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ህጋዊ ሰውነት እንዲሰጠው የተዘጋጀ ረቂቅ አዋጅ አንዱ ነበር። የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የረቂቅ አዋጁ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መመራቱንና ሌሎች ወቅታዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል። የምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር እንድሪስ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የምክር ቤቱ የህጋዊ ሰውነት ጥያቄ ከቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግስት ጀምሮ ሲቀርብ ነበር። ለዓመታት ሲንከባለል የቆየውና የፍትህና የእኩልነት ጥያቄ የነበረውን በአሁኑ ወቅት መንግስት ለመመለስ ያሳለፈውን ውሳኔም አድንቀዋል። እንዲሁም የሙስሊም ባንክ እንዲቋቋም ከመፍቀድ ጀምሮ በርካታ የህዝበ ሙስሊሙ ጥያቄዎች በአሁኑ ወቅት በስልጣን ላይ ባለው መንግስት አማካኝነት ምላሽ ማግኘታቸውን ገልጸዋል። ህዝበ ሙስሊሙን ያስደሰተው ጉዳይ ህዝበ ክርስቲኑንም የሚያስደስት እንደሚሆን ተናግረዋል። ፕሬዚዳንቱ ረቂቅ አዋጁ በአፋጣኝ ጸድቆ ጥቅም ላይ ይውል ዘንድም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ትኩረት እንዲሰጠው ጠይቀዋል። የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ህጋዊ ሰውነት አለማግኘት የሙስሊሙን ኀብረተሰብ ጥቅም በሚፈለገው ልክ ለማስጠበቅ ሳይቻል መቆየቱም ተገልጿል። የጠቅላይ ምክር ቤቱ ዋና ጸሓፊ ሼህ ቃሲም መሐመድ ታጁዲን የምክር ቤቱ ህጋዊ ሰውነት አለማግኘት ሙስሊሙ መንፈሳዊ ኃላፊነቱን በአግባቡ እንዳይወጣ ማድረጉን ገልጸው፤ በተለይ ከሃጂና ኡምራ ጉዞ ጋር ተያይዞ በሚፈለገው ልክ መንቀሳቀስ አለመቻሉን አመልክተዋል። በተጨማሪም እስላማዊ ተቋማት እንዳይመሰረቱና እስላማዊ ታሪኮችና ቅርሶችን በመንከባከብ ረገድ ችግር ሆኖ እንደነበር ተናግረዋል። ''ህጋዊ ሰውነት ለማግኘት የተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መመራቱ ሕዝበ ሙስሊሙ በአንድነት ለአገር ጥቅም እንዲሰራ ትልቅ አቅም ይሆነዋል'' ብለዋል። በተያየዘም በሞጣ ከተማ በደረሰው ጥቃት ለጉዳት የተዳረጉትን ለማገዝ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር አስመልክቶ ጠቅላይ ምክር ቤት መግለጫ ሰጥቷል። መግለጫውን የሰጡት የምክር ቤቱ ምክትል ቦርድ ሰሳቢና የሞጣ ጉዳይ አብይ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሼህ ኑረዲን ደሊል ተጎጂዎቹ እስካሁን አስፈላጊውን ድጋፍ እንዳላገኙ ጠቁመዋል። የከተማው ሙስሊሞች የመስገጃና ሌሎች ሃይማኖታዊ ጉዳዮች ማስፈጸሚያና መተዳደሪያ ቦታ በማጣታቸው ምክር ቤቱ ገቢ ለማሰባሰብ መወሰኑን ተናግረዋል። በዚሁ መሠረት ከጥር 22 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ የመርሃ ግብሩ የመጀመሪያ ዙር መካሄድ እንደሚጀምር ገልጸዋል። ድጋፍ ማድረግ የሚፈልጉ ወገኖችም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሂሳብ ቁጥር 1000315148457 ተጠቅሞ ገንዘብ ገቢ ማድረግ እንደሚችል ተገልጿል። በቦታው የደረሰውን ጉዳት የሚያጣራ ገለልተኛ ኮሚቴ እስካሁን አለመቋቋሙን ያመለከተው የምክር ቤቱ መግለጫ፤ የፌዴራል መንግስት ገለልተኛ ቡድን ወደ ስፍራው እንዲልክ ጠይቋል። ጠቅላይ ምክር ቤቱ ባለፈው ሳምንት የጥምቀት በዓል በጎንደር ከተማ ሲከበር በደረሰው ጉዳት ህይወታቸውን ላጡና ለተጎዱ ወገኖች ጥልቅ ሐዘን እንደተሰማው ገልጿል።