ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት የወረታ ደረቅ ወደብ በሚቀጥለው ሳምንት ይመረቃል

አዲስ አበባ፣ ጥር 16/2012 (ኢዜአ) ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገበትና የሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያን የወጪና ገቢ ንግድ ያሳልጣል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት የወረታ ደረቅ ወደብ የመጀመሪያ ምዕራፍ በሚቀጥለው ሳምንት ይመረቃል። የኢትዮጵያ ባህርና ትራንስፖርት ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት የወደብና ተርሚናል ዘርፍ ምክትል ዋና ስራ ስፈጻሚ አቶ እውነቱ ታዬ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የወደብ ልማቱ አገሪቱ ያላትን የደረቅ ወደብ ቁጥር ወደ ስምንት ከፍ ያደርገዋል። በአጠቃላይ 25 ሄክታር መሬት ሽፋን የሚኖረው የወረታ ደረቅ ወደብ በመጀመሪያው ምዕራፍ ሶስት ሄክታር መሬት ግንባታ ተጠናቆ በሚቀጥለው ሳምንት እንደሚመረቅ ተናግረዋል። ቀሪው ሔክታር በቀጣዮቹ አመታት የሚለማ ሲሆን አገሪቱ ያላትን የደረቅ ወደብ የማስተናገድ አቅም በስምንት እጥፍ ያሳድገዋል ተብሎ ይጠበቃል። የወረታ ደረቅ ወደብ ለሰሜን ምዕራብ የሀገሪቱ አካባቢ የወጪና ገቢ ንግድን ለማስተናገድ የሚያገለግል ሲሆን፣ አገልግሎት ፈላጊው የነበረበትን እንግልት ይቀንሳል ተብሏል። በሚያዝያ ወር 2011 ዓ.ም  ግንባታው የተጀመረው የወረታ ደረቅ ወደብ ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጎበታል። ደረቅ ወደቡ ከሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ ወደ ውጭ የሚላኩና ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ምርቶችን ለአካባቢው የንግድ ማህበረሰብ ለማቅረብም አገልግሎት ይሰጣል። ይህም የመልቲ ሞዳል አገልግሎት ለማግኘት ወደሌሎች አካባቢዎች በመሄድ ይባክን የነበረውን የጊዜና ገንዘብ ወጪ እንደሚቀንስ ተናግረዋል። እንደ ምክትል ስራ አስፈጻሚው ገለጻ፤ በኢትዮጵያ እያደገ የመጣውን የንግድና የምጣኔ ሃብት እንቅስቃሴ ታሳቢ በማድረግ የደረቅ ወደብ ልማት በተለያዩ አካባቢዎች እየተከናወነ ነው። በአሁኑ ጊዜ የድሬዳዋ ደረቅ ወደብ በግንባታ ላይ የሚገኝ ሲሆን የመቀሌ ደረቅ ወደብ ማስተር ፕላንን በዚህ አመት በማጠናቀቅ በቀጣይ አመት ግንባታው እንደሚጀመር ጠቁመዋል። የሞጆ ደረቅ ወደብን ዋና ማዕከል ለማድረግ 100 ሚሊዮን ብር ተመድቦ እየለማ ሲሆን ከአለም ባንክ በተገኘ 150 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ተጨማሪ 30 ሔክታር ለማልማት እየተሰራ እንደሆነ ገልጸዋል። በመሆኑም የወጪና ገቢ ንግድን በማቀላጠፍ በጂቡቲ ለወደብ ኪራይ ይወጣ የነበረውን ገንዘብና እንግልትን እንዲቀንስ ለማድረግ እየተሰራ እንደሆነ ጠቁመዋል። እያንዳንዱ አስመጪ ያመጣውን ኮንቴነር በ15 ቀን ጊዜ ውስጥ ከደረቅ ወደቡ ማንሳት የሚጠበቅበት ቢሆንም ኮንቴነሮች በደረቅ ወደብ ለአመታት እንደማይነሱ በተደጋጋሚ የሚገለጽ ሲሆን ችግሩ በመንግስት ተቋማት ላይ በስፋት ይስተዋላል። ምክትል ስራስፈጻሚው አቶ እውነቱ ''በአሁኑ ወቅት ረዥም ጊዜ የቆዩ ኮንቴነሮች እንዲወጡ ግፊት እየተደረገ ነው'' ብለዋል። ኢትዮጵያ የባህር በር ያሌላት አገር በመሆኗ ለወደብ ኪራይ የሚወጣውን በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር ለማስቀረት ባለፉት 11 አመታት የደረቅ ወደብ ግንባታ ላይ ትኩረት አድርጋለች። የወደብ መቋቋም ለአካባቢው ማህበረሰብ የስራ እድል ከመፍጠር ባለፈ ለንግድና ኢንቨስትመንት መነቃቃት የሚኖረው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው። ሞጆ፣ ቃሊቲ፣ ገላን ሙሉ በሙሉ አግልግሎት እየሰጡ የሚገኙ ደረቅ ወደቦች ናቸው።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም