ቀጥታ፡

የኢትዮጵያና ቻይና ትብብር የጋራ ጥቅማቸውን መሰረት ያደረገ ነው ... በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር

አዲስ አበባ፤ ጥር 16/2012 (ኢዜአ) ኢትዮጵያና ቻይና በተለያዩ ዘርፎች ላይ የሚያደርጉት ትብብር የጋራ ጥቅማቸውን መሰረት ያደረገ መሆኑን በኢትዮጵያ የአገሪቱ አምባሳደር ታን ጂያን ገለጹ። የአገሮቹ የንግድና ኢንቨስትመንት መጠን ሶስት ቢሊዮን ዶላር ደርሷል። የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን መረጃ እንደሚያመለክተው ወደ ኢትዮጵያ ከሚመጡ ቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንቶች ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዘው የቻይናውያኑ ነው። ቻይና በኢትዮጵያ ከሚካሄደው እንደ መንገድ፣ ባቡርና ኢንዱስትሪ ፓርኮች መሰረተ ልማት ግንባታ ቻይና ትልቁን ድርሻ ትይዛለች። ጨርቃ ጨርቅና አልባሳት፣ ግንባታ፣ ማምረቻ ኢንዱስትሪ፣ ምግብ ማቀነባበር፣ ሆቴልና ቱሪዝም ቻይናውያን ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ተሳትፎ እያደረጉባቸው ከሚገኙ ዘርፎች መካከል ይጠቀሳሉ። በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ታን ጂያን ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ ኢትዮ-ቻይና በተለያዩ ዘርፎች ያላቸው ትብብር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጎለበተ መጥቷል። አገሮቹ በህዝብ ለህዝብ፣ በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ እንዲሁም በባህል ጠንካራ ወዳጅነት መመስረታቸውንም ተናግረዋል። ይህ ትብብር የሁለቱንም የጋራ ጥቅም መሰረት ያደረገ መሆኑን የገለጹት አምባሳደር ታን ጂያን፤ ትብብሩ ከሁለትዮሽ ባለፈ ስትራቴጂካዊ መሆኑን ተናግረዋል። እ.አ.አ በ2018 የሁለቱ አገሮች የንግድና ኢንቨስትመንት መጠንም ሶስት ቢሊዮን ዶላር መድረሱን አምባሳደሩ አመልክተዋል። የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነቱን ወደ ላቀ ደረጃ በማሸጋገር የኢኮኖሚ ትስስራቸውን የበለጠ ለማጠናከር እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል። አገሮቹ የስፔስ ሳይንስን ጨምሮ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፎች ያላቸውን ትብብር የበለጠ እንደሚያጠናክሩም አምባሳደሩ አስታውቀዋል። በተያዘው የፈረንጆቹ ዓመት አገሮቹ መደበኛ የሁለትዮሽ ግንኙነት የጀመሩበትን 50ኛ ዓመት በዓል ያከብራሉ። ዝግጅቱ የህዝብ ለህዝብ ትስስሩን ከማጠናከር ባለፈ በተለያዩ ዘርፎች ላይ ያላቸውን ትብብር የበለጠ በሚጠናከርበት መልኩ በአዲስ አበባና በቤጂንግ ይከበራል።          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም