በዞኑ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ተጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
በዞኑ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ተጀመረ
ደብረ ማርቆስ ጥር 15 /2012 በምሥራቅ ጎጃም ዞን የዚህ ዓመት የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ በይፋ ተጀመረ። እስከ የካቲት 30 ቀን 2012 ድረስ የሚቆየው ሥራ ትናንት የተጀመረው በማቻከል ወረዳ በምንጭ የቀስት ቀበሌ ነው። ሥራው ከ620ሺህ ሕዝብ በማሳተፍ ከ61ሺህ ሄክታር በላይ መሬት የተፈጥሮ ሃብት ልማት ለማከናወን ግብ እንደተያዘ የዞኑ ግብርና መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ አንዳርጋቸው ልየው አስታውቀዋል። ሥራው በ998 ተፋሰሶች ላይ እንደሚከናወን የገለጹት አቶ አንዳርጋቸው፣ለዚህም ቀያሽ አርሶ አደሮችን መሰልጠናቸውና ከ33ሺህ በላይ መስሪያ ቁሳቁስ መቅረባቸው ተናግረዋል። የዞኑ ምክትል አስተዳደሪ አቶ ኑርልኝ ብርሃኑ በበኩላቸው ሥራው የአርሶ አደሩን ዘላቂ ተጠቃሚነትና ምርታማነትን ለማሳደግ አስችሏል ይላሉ። ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ ተግባራት ምርታማነት ማደጉንና አርሶ አደሩ በዘመናዊ መሣሪያዎች ተጠቅሞ ለማረስና ምርቱን የመሰብሰብ ፍላጎት እንዳሳደረበት ገልጸዋል። የማቻክል ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር አየለ ጥሩሰው ባለፉት ዓመታት ባካሄዱት ሥራ ከግማሽ ሄክታር ማሳ ላይ ያገኙት የነበረው ምርት አሁን እስከ ሶስት ኩንታል ጭማሪ እንዳሳየ አስታውቀዋል። በተጨማሪም ከብቶቻቸውን በለሙ ተፋሰሶችና በማሳቸው ድንበር ሳር እያጨዱ በማድለብ በዓመት እስከ 40ሺህ ብር ገቢ ማግኘታቸውን ተናግረዋል።በዙሁ ወረዳ የምንጭቀስት ቀበሌ ነዋሪ ወጣት እኔማየሁ ደምሴ በበኩሉ በሥራው የለሙ ተፋሰሶች በመጠቀም ንብ በማነብ ኑሮዬን ለማሻሻል በቅቻለሁ በማለት በኑሮው ያገኘውን ለውጥ አሳይቷል። "መሬት የሌለን ሶስት ጓደኛሞች ተደራጅተን በለሙ ተፋሰሶች በንብ ማነብ ሥራ በመሰማራት በዓመት ለእያንዳንዳችን ከ20 ሺህ ብር በላይ ከማር ሽያጭ እያገኘን ነው" ብሏል። አሁን ከንብ ማነብ በተጨማሪ ከተፋሰሱ ሳር በማጨድና በመቀለብ 30 በጎችን በማድለብ ላይ እንደሚገኝ ገልጿል። በዞኑ በሥራው ጥበቃ የተደረገላቸው ከ890 በላይ ተፋሰሶች እንደሚገኙ ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመላክታል።