በምስራቅ ሐረርጌ ዞን የሚመረተው ቡና ለዓለም ዓቀፍ ገበያ እየቀረበ አይደለም ተባለ - ኢዜአ አማርኛ
በምስራቅ ሐረርጌ ዞን የሚመረተው ቡና ለዓለም ዓቀፍ ገበያ እየቀረበ አይደለም ተባለ
ሀረር ሰኔ 18/2010 በምስራቅ ሐረርጌ ዞን የሚመረተው ቡና ዓለም አቀፍ ገበያን እያገኘ እንዳልሆነ የዞኑ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ገለፀ፡፡ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ድርጅት በዞኑ ውስጥ የሚገኙ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የስራ እንቅስቃሴ በኃላፊዎችና በመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ተጎብኝተዋል። የዞኑ ቡናና ሻይ ባለስልጣን የስራ ሂደት መሪ አቶ አብደላ አብደሽ እንደገለጹት፤ በዞኑ 60 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ከሚገኘው የቡና ተክል 27ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ያለው ቡና ምርት የሚሰጥ ቢሆንም ምርቱ ተገቢውን አለም አቀፍ ገበያ እያገኘ አይደለም። በዘንድሮው አመት ከ12ሺህ ቶን በላይ ቡና ምርት መገኘቱን የገለጹት አቶ አብደላ የገበያ ትስስር የተፈጠረው 2ሺህ922 ቶን ለሚሆነው ብቻ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ የቡና ምርቱ ከተያዘው ዕቅድ ውስጥ 33 በመቶ ብቻ ለዓለም ለዓቀፍ ገበያ መቅረብ ባለመቻሉን ገልጸዋል፡፡ ለገበያ መቅረብ ያልቻለው ምርትም በአምራች አርሶ አደሮች፣ በነጋዴውና በማህበራት እጅ እንደሚገኝም አቶ አብደላ ተናግረዋል፡፡ በቂ የሆነ የገበያ ዕድል ባለመኖሩ ቡና በማምረት የተሰማሩ አርሶ አደሮች፣ ቡና በመነገድ የተሰማሩ ነጋዴዎችና ማህበራት ተስፋ ወደመቁረጥ እየገቡ እንደሆነ ጠቅሰዋል። አንዳንድ የቡና አምራች ገበሬዎችም የጫት ምርትን በአማራጭነት ማየት መጀመራቸውንም ገልጸዋል፡፡ ችግሩን ለመቅረፍ የቡና ነጋዴዎችን በማህበራት በማደራጀት ወደ ውጪ አገሮች እንዲልኩ ጥረት ተደርጎ የነበረ ቢሆንም በአቅም ማነስ ምክንያት እንዳልተሳካ አቶ አብደላ ተናግረዋል፡፡ ስለሆነም መንግስት በዞኑ የሚመረተው ቡና ተገቢውን አለም አቀፍ ገበያን እንዲያገኝ ጥረት ማድረግ እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን በቀጣይ ከአምስት እስከ አስር አመት ውስጥ የዞኑ ቡና ምርት ሊጠፋ እንደሚችል ያላቸውን ስጋት አቶ አብደላ ተናግረዋል፡፡