በአገሪቱ የሚስተዋለው የሰላም እጦት የንግዱ ዘርፍ ላይ ጫና ማሳደሩ ተገለጸ

123

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 15/2012 በተለያዩ ወቅቶች በአገሪቱ ተከስተው በነበሩ ግጭቶች ምክንያት የንግድ እንቅስቃሴው ጫና ውስጥ በመግባቱ ኢኮኖሚው እንዲዳከም አድርጓል ሲሉ ባለኃብቶችና የንግዱ ማህበረሰብ አባላት ተናግረዋል። ይህ የተባለው የአዲስ አበባ ንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት በኢትዮጵያ ወቅታዊ የኢኮኖሚ ሁኔታዎች ላይ ከባለኃብቶችና ከንግዱ ዘርፍ ማህበረሰብ ጋር ባደረገው የውይይት መድረክ  ላይ ነው።

ውይይቱ በየጊዜው በሚከሰቱ ፖለቲካዊ ሁኔታዎችና አለመረጋጋቶች የተነሳ ኢኮኖሚው በሚፈለገው መልኩ አለመንቀሳቀሱን ተከትሎ በተስተዋለው የኢኮኖሚ መዳከም ላይ መፍትሄ ለማበጀት ያለመ ነው።

የውይይት መነሻ ጽሁፍ ያቀረቡት የምጣኔ ኃብት ባለሙያ አቶ ሰይፈ አያሌው በአገሪቱ በተከሰተው አለመረጋጋት የተነሳ በርካታ የንግድና የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች መስተጓጎላቸውን ገልጸዋል።

አለመረጋጋቱ በተለያዩ ዘርፎች የተሰማሩ አቅራቢዎች ለኪሳራ ሲዳረጉ ተገልጋዮችም በአቅርቦት ችግር ለአላስፈላጊ እንግልት እንዲዳረጉ ምክንያት ሆኗል።

በዋናነትም አገሪቱ ከዘርፉ ማግኘት ያለባትን ገቢ እንድታጣና የኢኮኖሚው እንቅስቃሴ እንዲዳከም ማድረጉንም ገልጸዋል።

ይህንንም ተከትሎ በርካታ አልሚዎች ከነበሩበት ዘርፍ እንዲያፈገፍጉና በስራቸው የነበሩትን ተቀጣሪዎች ለማሰናበት መገደዳቸውንም አክለዋል።

የ'ሴንተር ፎር ኢንተርናሽናል ፕራይቬታይዜሽን ዓለም አቀፍ ድርጅት' የምስራቅ አፍሪካ ዳይሬክተርና  የውይይቱ ተሳታፊ አቶ ኃይለመለኮት አስፋው ተከስቶ በነበረው የሰላም እጦት በርካታ የልማት እንቅስቃሴዎች በመጓተታቸው አላስፈላጊ ውድመትና ኪሳራ ማጋጠሙን ገልጸዋል።

ዜጎች በአሁኑ ወቅት ከፖለቲካ ጉዳይ ይልቅ ለኢኮኖሚ ጥያቄ ቅድሚያ በመስጠት የተጀመረውን ልማትና እድገት በጋራ ማፋጠን እንደሚያስፈልግ የውይይቱ ተሳታፊዎች አመላክተዋል።

ኢኮኖሚውን ለመደገፍ የሚመለከታቸው አካላት የአገሪቱን የኢኮኖሚ ሁኔታ ለማስገንዘብ መትጋት እንዳባቸውም አመልክተዋል።

በተጨማሪም የፖለቲካ ጥያቄን አስታከው በንብረት ላይ ውድመት በሚያደርሱና የንግዱን እንቅስቃሴ በሚያውኩ አካላት ላይ ህጋዊ እርምጃ የመውሰድ ተግባር በትኩረት ሊሰራበት እንደሚገባ የብሌስ አግሪ ፉድ ኩባንያ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ግርማ ማሞ ጠቁመዋል።

የመሬት ፖሊሲ አለመሻሻል፣ የፋይናንስ አቅርቦት እጥረት፣ የውጪ ምንዛሪ እጥረትና ግምታዊ የታክስ አጣጣል በንግድ ዘርፉ ላይ ተጽእኖ እያሳደረ መሆኑንም አመልክተዋል።

ኢኮኖሚው እንዲያንሰራራ ለማድረግ በየዘርፉ ያሉ አካላት ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ እንደሚገባም የውይይቱ ተሳታፊዎች መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

የምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ወይዘሮ መሰንበት ሸንቁጤ ''የሰላም እጦቱ በኢኮኖሚው ላይ ያሳደረውን ጫና ከግምት በማስገባት ከመንግስት አካላት ጋር ተከታታይ ውይይት የማድረግና የመፍትሄ አቅጣጫ የመፈለግ ተግባር እየተከናወነ ነው'' ብለዋል።

የንግድ ፖሊሲውን ለማሻሻል ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው "ቢዝነስ ለሰላም ሰላም ለቢዝነስ" በሚል መርህ የአሰራር ስርዓት ለመዘርጋት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይም ሰላምን ለማምጣት ኢኮኖሚው ላይ መሰራት እንዳለበትና ዜጎች የኢኮኖሚ ችግር ጥያቄ እንዳይኖራቸው ማድረግ የሚያስፈልግ መሆኑን ጠቁመዋል።

በተለይም ወጣቱ የስራ እድል የሚያገኝበትን ምቹ ሁኔታ መፍጠርና የአገሪቱን ኢኮኖሚ ወደ ተሻለ ደረጃ በማሳደግ የሰላም እጦት እንዳይከሰት ማድረግ እንደሚባ ተናግረዋል።

እነዚህንና ሌሎች መሰረታዊ ጉዳዮችን ለመመለስ ምክር ቤቱ ከመንግስት ጋር እንደሚሰራ ወይዘሮ መሰንበት አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም