ኢትዮጵያና ጅቡቲ የንግድ ዘርፍ ትብብራቸውን ይበልጥ ለማጠናከር እየሰሩ ነው

91
አዲስ አበባ ጥር 15/ 2012(ኢዜአ) በጅቡቲ ንግድ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት የተመራ የንግድ ልዑካን ቡድን ከኢትዮጵያ መንግስት ተቋማት ኃላፊዎችና የክልል አመራሮች ጋር ዛሬ የሞጆ ደረቅ ወደብን ጎብኝቷል። የጅቡቲው ንግድ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት የሱፍ ሙሳ በዚሁ ጊዜ "ኢትዮጵያ የባህር በር ባይኖራትም በደረቅ ወደብ የምታከናውነው የስራ እንቅስቃሴ የሚበረታታ ነው" ብለዋል። የሞጆ ደረቅ ወደብ የባህር መውጫ በር ለሌላቸው የጎረቤት አገራት እንደ ደረቅ ወደብም ለማገልገል ይችላል የሚል እምነት እንዳላቸውም ተናግረዋል። ሁለቱ አገራት በምጣኔ ሃብት፣ በንግድና በሎጂስቲክስ ዘርፍ በቀጣይ የተጠናከረ ስራ እንደሚያከናውኑም አስታውቀዋል። የጅቡቲ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ የሚገኙ የኢንቨስትመንት አማራጮችን በመመልከት የሚሰሩበት ሁኔታ መኖሩንም አክለዋል። የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ምክትል ፕሬዚዳንት ልዩ አማካሪ አሚን ጁንዲ በበኩላቸው ኢትዮጵያና ጅቡቲ በሎጂስቲክስ ዘርፍ ያላቸውን ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር እንደሚሰሩ ተናግረዋል። የጅቡቲ ባለሃብቶች የኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት አማራጮች በመለየት መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ የማስተዋወቅ ስራ እንደሚሰራም ገልጸዋል። የጅቡቲ የንግድ ልዑካን ቡድን የአዳማ፣ የዱከም ኢስተርን ኢንዱስትሪ ፓርክና ሌሎች የኢንዱስትሪ ማዕከላትን እንደሚጎበኙ ይጠበቃል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም