ዛሬ ማለዳ በተካሄደው የዱባይ ማራቶን ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሁሉቱም ፆታ ድል አድርገዋል

ኢዜአ ጥር  15/2012   በስታንዳርድ ቻርተርድ ዱባይ ማራቶን 2020 ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሁለቱም ፆታዎች በማሸነፍ የበላይነቱን ወስደዋል፡፡ በሴቶች በተደረገው ውድድር ወርቅነሽ ደገፋ በ (2:19:38) ጊዜ ሩጫውን አንድኛ ሆና ስታጠናቅቅ ጉተኒ ሾኔ ( በ2:20:11) እና በዳቱ ሂርጳ ሁለተኛ(2:21:55 ) እና ሶስተኛ ደረጃን ይዘው ውድድሩን ፈጽመዋል፡፡
አትሌት ወርቅነሽ ደገፋ እኤአ 2017 የዱባይ ማራቶን ባለድል መሆኗ ይታወሳል፡፡ በሴቶቹ ውድድር ከአራት እስከ ዘጠኝ ያለውን ደረጃ የያዙትም ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ናቸው፡፡ በወንዶች በተካሄደው ውድድር አትሌት አዱኛ ቢቂላ ሲያሸንፍ ሁለት ሰዓት ከስድስት ደቂቃ ከ15 ሴኮንድ (2:06:15) የገባበት ሰዓት ነው፡፡ ኬንያዊው ኤሪክ ኪፕታኑይ አዱኛን ተከትሎ በ2:06:17 ሁለተኛ ደረጃ ውጥቷል፡፡ አበጀ አያና ደግሞ ኬንያዊውን ተከትሎ በ 2:06:18 ጊዜ ውድድሩን በሶስተኝነት ፈፅሟል፡፡ የባለፈው አመት የዱባይ ማራቶን አሸናፊ ሄታነህ ሞላ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ከአራት እስከ ሀያ ያለውን ደረጃም የያዙት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ናቸው፡፡ የዱባይ ማራቶን እኤአ 2000 ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ኢትዮጵያ በሴቶች ለ15ኛ ጊዜ በወንዶች ለ14ኛ ጊዜ በማሸነፍ የበላይነቱን ይዛለች፡፡ የዱባይ ማራቶንን ለመጀመሪያ ጊዘ ያሸነፈው ኢትዮጵያዊ አትሌት ጋሻው አስፋው ሲሆን እኤአ 2004 ነበር፡፡ በተመሳሳይ ወቅት በሴቶች ያሸነፈችው አትሌት ደግሞ ሌይላ አማን መሆኗ አይዘነጋም፡፡ ለውድድሩ አንደኛ አሸናፊዎች 100ሺህ ዶላር በሽልማት መልክ ቀርቧል፡፡ ምንጭ፡ካሌጅ ታይምስ
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም