የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 10ኛ ሳምንት ጨዋታዎች የፊታችን ቅዳሜና እሁድ ይካሄዳሉ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 10ኛ ሳምንት ጨዋታዎች የፊታችን ቅዳሜና እሁድ ይካሄዳሉ
አዲስ አበባ ጥር 14/2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 10ኛ ሳምንት ጨዋታዎች የፊታችን ቅዳሜና እሁድ ይካሄዳሉ። የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 10ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ላይ ደርሷል። ጨዋታዎቹም በተያዘላቸው የውድድር መርሀ-ግብር መሰረት የፊታችን ቅዳሜና እሁድ ማለትም ጥር 17 እና 18 ቀን 2012 ዓም በአዲስ አበባ እና በክልል ስታዲየሞች ይደረጋሉ። በዚህም ቅዳሜ በ9:00 ሰዓት ስሁል ሽረ ከጅማ አባጅፋር ክልል ላይ የሚደረግ ጨዋታ ሲሆን ሰበታ ከተማ ከሃዋሳ ከተማ ደግሞ በአዲስ አበባ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። እሁድ በሚደረጉ ጨዋታዎች ደግሞ ወላይታ ዲቻ ከመቀለ ሰብአ እንደርታ፣ ወልቂጤ ከተማ ከድሬዳዋ ከተማ፣ አዳማ ከተማ ከሃዲያ ሆሳዕና፣ ወልዋሎ አዲግራት ከኢትዮጵያ ቡና፣ ፋሲል ከነማ ከሲዳማ ቡና እንዲሁ በተመሳሳይ በ9:00 ሰዓት በክልል ይጫወታሉ። ቅዱስ ጊዮርጊስና ባህርዳር ከተማ ደግሞ በአዲስ አበባ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። በፕሪሚየር ሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ መሰረት መቀለ ሰብአ እንደርታ በ19 ነጥቦች እየመራ ሲሆን ፋሲል ከነማ እና ስሁል ሽረ በእኩል 15 ነጥብ ሁለተኛ እና ሶስተኛ ሆነው ይከተላሉ። ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ባህር ዳር ከተማ ደግሞ እኩል 14 ነጥብ ይዘው ከ4 እስከ 6 ያለው ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። አዳማ ከተማ፣ ሀዲያ ሆሳዕናና ወልቂጤ ከተማ ከ14 እስከ 16 ደረጃ ይዘው በሊጉ ግርጌ ስር ይገኛሉ።