ኢትዮጵያ በጥናት የተቃኘ የፍልሰት ፖሊሲ ሊኖራት ይገባል ተባለ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በጥናት የተቃኘ የፍልሰት ፖሊሲ ሊኖራት ይገባል ተባለ
አዲስ አበባ ጥር 14/2012 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ የስደተኞችን ጉዳይ የምታስተናግድበት በጥናት ላይ የተመሰረተ የፍልሰት ፖሊሲ ሊኖራት እንደሚገባ ተጠቆመ። ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ያዘጋጃው አውደ ጥናት ዛሬ በአዲስ አበባ ተጀምሯል። ከስደት ጋር በተያያዘ የሚመለከታቸው የመንግሥትና ዓለም አቀፍ ተቋማት በጋራ መስራት የሚችሉበትን ሁኔታ ማመቻቸት የአውደ ጥናቱ ዋና ግብ ነው። በአውደ ጥናቱ ላይ የሕገ ወጥ ስደት አሉታዊ ጫናዎችና የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ጨምሮ የተግባሩ ተለዋዋጭ ገጽታዎችን የሚጠቁሙ በርከት ያሉ የጥናት ውጤቶች እንደሚቀርቡም ነው የተገለጸው። ከኢትዮጵያ በየዓመቱ 200 ሺህ ወጣቶች በተለያዩ መውጫ ድንበሮች እንደሚወጡ የዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት መረጃ ያመለክታል። ድንበር አቋርጠው ወደሌሎች የዓለም ክፍሎች በህገ ወጥ መንገድ የሚሰደዱት ሴቶችና የህጻናት ቁጥር እየጨመረ መሄድ ጉዳዩን የበለጠ አሳሳቢ እያደረገው መሆኑ ተጠቁሟል። በዋናነት የኢኮኖሚ ጉዳይ ለፍልሰቶች መንስኤ ቢሆንም የአቻ ግፊት፣ የቤተሰብ ሞት፣ ለሕገ ወጥ ሰው አዘዋዋሪዎች አትራፊ የሥራ መስክ መሆኑ ለመባባሱ ምክንያት ናቸው ተብሏል። የዓለም አቀፉ ስደተኞች ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይ ማላንቦ ሙንጋ እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ችግሩን በመከላከል በኩል አበረታች ተግባራትን እያከናወነ ነው። ይሁን እንጂ በመረጃና በጥናት ላይ የተመሰረተ የፍልሰት ፖሊሲ አለመኖር ችግር መፍጠሩን ጠቅሰው ይህም በሚመለከታቸው አካላት ተገቢው እርምጃ እንዳይወሰድ እንቅፋት ፈጥሯል ብለዋል። ኢትዮጵያ የችግሩን ውስብስብነት በአግባቡ በመለየትና ከተጎጂዎቹ የሚገኘውን መረጃ በመጠቀም ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ መዘየድ ይቻል ዘንድ መስራት እንደሚገባ አመላክተዋል። ''የኢትዮጵያ መንግሥት መረጃ ላይ የተመሰረተ ፖሊሲ ለማውጣት ከጥናትና ምርምር ተቋማት ጋር በመቀናጀት መስራት ይጠበቅበታል'' ሲሉም የዓለም አቀፉ ስደተኞች ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይ ማላንቦ ሙንጋ የሚገልፀጹት። መሰል አውደ ጥናቶችም ለፖሊሲ ቀረፃው ግብዓት እንደሚገኝባቸው አክለዋል። አጥኚዎችም ችግሩን ለመከላከል የትኞቹ አከባቢዎች ላይ ትኩረት በመስጠት መስራት ይገባል በሚለው ላይ እንዲያተኩሩም መክረዋል። ዓለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅትም ኢትዮጵያ ህገ ወጥ ስደትን በመከላከል ረገድ በመረጃ ላይ የተመሰረተ ተግባር ማከናወን እንድትችል አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል። የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሕገ ወጥ የሰራተኛ ምልመላ መከላከያ ቡድን መሪ አቶ ዘርይሁን የሺጥላ በበኩላቸው መንግሥት የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት ሕገ ወጥ ተከላካይ ግብረ ኃይል ከሟቋቋም ጀምሮ አዋጆችን የማሻሻል እርምጃዎች እየወሰደ መሆኑን ገልጸዋል። በተለይም የፍልሰት ፖሊሲ አስፈላጊነት ከግምት ውስጥ በማስገባት ፖሊሲ ለማውጣት እንቅስቃሴ ተጀምሯል ያሉት ቡድን መሪው ፖሊሲውን የሚያዘጋጅ የቴክኒክ ኮሚቴ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን መቋቋሙን ጠቁመዋል። ኮሚቴው የሌሎች አገራት ፖሊሲ፣ ተሞክሮና ልምድ እየቃኘ መሆኑን ጠቁመው የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ ያገናዛበ ፖሊሲ ለማውጣት ምን ምን ጉዳዮችን ሊያካተት ይገባል? የሚለው እየታየ ነው ብለዋል። እንደ አቶ ዘሪሁን ገለጻ ከአገር ውስጥ ጀምሮ እስከ ተቀባይ አገራት ድረስ ያሉ የሕገ ወጥ ደላላ መረቦችን በመከተል እርምጃ እየተወሰደ ነው። በአውደ ጥናቱ ዩኒቨርስቲዎች፣ ምሁራን፣ የጥናትና ምርምር ተቋማት፣ ግብረ ሰናይ ድርጅቶችና ፖሊሲ አውጪዎች እየተሳተፉበት ሲሆን ነገም ቀጥሎ እንደሚውል ተገልጿል።