ቀጥታ፡

የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ኃላፊነቱን በአግባቡ መወጣት ይጠበቅበታል ... የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

አዲስ አበባ፤ ጥር 14/2012 (ኢዜአ)  የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ከመንግስትና ከሕዝብ የተጣለበትን ኃላፊነት በአግባቡ እንዲወጣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳሰበ። ዋና ኮሚሽነሩ ዶክተር ዳንኤል በቀለ በበኩላቸው ከተቋቋመ 15 ዓመታትን ያስቆጠረው ኮሚሽን በአግባቡ የተደራጀ ባለመሆኑ ተልዕኮውን መወጣት አልቻለም ብለዋል። ኮሚሽኑ ዛሬ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀረበው የስድስት ወራት ስራ አፈፃፀም ሪፖርት የአገሪቷን ወቅታዊ ሁኔታ ያላሳየና በሚፈለገው ልክ የተደራጀ አይደለም ተብሏል። በአገሪቷ የሚታዩ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በመፈተሽና በዜጎች ላይ የሚደርሰውን መፈናቀል በመገምገም ሪፖርት አለማቅረቡም በምክር ቤቱ ዘንድ በክፍተት ተወስዷል። በተለይም ክትትል ባደረገባቸው ማረሚያ ቤቶችና ፖሊስ ጣቢያዎች የተመለከታቸውን የሰብዓዊ መብት አያያዝ በጎ ጎኖችም ሆነ ክፍተቶች በሪፖርቱ በግልጽ ማስቀመጥ ነበረበት ነው የተባለው። ኮሚሽኑ ባለፉት ስድስት ወራት የሰብዓዊ መብቶችን አስመልክቶ ለሕብረተሰቡ የሰጠው ስልጠና ያመጣውን ተጨባጭ ውጤት በዝርዝር ማቅረብ እንደነበረበትም ተነግሯል። በአገሪቷ የተለያዩ አካባቢዎች ያለውን የፀጥታ ችግርና በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሴቶች ላይ የሚደርሱ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ጨምሮ የዜጎች መፈናቀል መነሻዎችን አስመልከቶ ሪፖርት ማቅረብ እንደነበረበትም ተጠቁሟል። ነገር ግን ኮሚሽኑ በተጠቀሰው ጊዜ በአገሪቷ አዲስ በሚወጡና ደረጃቸው በሚሻሻል አዋጆችና ደንቦች ላይ ሃሳብ በመስጠትና ሙያዊ ድጋፍ በማድረግ ያከናወናቸው ተግባራት በበጎ መልኩ ታይተዋል። በዚህ ረገድ የፀረ ሽብርና የጥላቻ ንግግር አዋጆች ላይ የነበረው ተሳትፎ በአብነት ተጠቅሷል። ዋና ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤል በቀለ ኮሚሽኑ ከተቋቋመ 15 ዓመታትን ቢያስቆጥርም በተገቢው መንገድ ባለመደራጀቱ የሚጠበቅበትን ተልዕኮ በአግባቡ መወጣት እንዳልቻለ ተናግረዋል። በአሁኑ ወቅትም ነፃ፣ ገለልተኛ፣ ብቃት ያለውና ጠንካራ ሆኖ እንዲደራጅ ስር ነቀል የአደረጃጀት ለውጥ እያካሄደ መሆኑንም ገልጸዋል። ሰብዓዊ መብትን በማስከበር ረገድ ዘላቂ ተቋም ለመገንባት ጥረት እየተደረገ መሆኑንም አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም