የህዳሴው ግድብ ተደራዳሪዎች ባበረከቱት አስተዋጽኦ የኢትዮጵያ ህዝብ ሊኮራ ይገባል-የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ምሁራን - ኢዜአ አማርኛ
የህዳሴው ግድብ ተደራዳሪዎች ባበረከቱት አስተዋጽኦ የኢትዮጵያ ህዝብ ሊኮራ ይገባል-የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ምሁራን
ባህርዳር ጥር 13/2012 (ኢዜና) የህዳሴው ግድብ ተደራዳሪዎች ባበረከቱት አስተዋጽኦ የኢትዮጵያ ህዝብ ሊኮራና ሊደግፋቸው እንደሚገባ በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የሲቪልና የውሃ ምህንድስና ምሁራን ገለጹ። ምሁራኑ ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ እንዳመለከቱት ተደራዳሪዎቹ በአሜሪካ የተካሄደው ድርድርና ስምምነት ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ በፍትሃዊነት የመጠቀም መብቷን አስከብረዋል። በግድቡ ዙሪያ የተካሄዱ ድርድሮችን በብቃት ያካሄዱትን የኢትዮጵያን ተደራዳሪዎች ሕዝቡ ሊደግፋቸው፣ ሊያበረታታቸውና ከጎናቸው ሊቆም ይገባል ብለዋል። በቀጣይም በአሜሪካ በሚካሄደው የመጨረሻ ስምምነት ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ የመጠቀም መብቷን በሚያስጠብቅ መልኩ ይፈጸማል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል። በዩኒቨርሲቲው የሲቪልና ውሃ ምህንድስና ፋካልቲ መምህርና ተመራማሪ ዶክተር አሰግደው ጋሻው፣ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ለቀጠናዊ ትስስርና ለጋራ ኢኮኖሚያዊ ብልጽግና አስተዋጽኦ እንዳለው ይገልጻሉ። ምንም እንኳ ግድቡ የተገነባው የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት ቢሆንም፤ ባለፉት ዓመታት በግድቡ ግንባታ ዙሪያ ከግብጽና ሱዳን ጋር ተከታታይ ድርድር በማድረግ ይህንኑ ጉዳይ ለማሳወቅ ጥረት መደረጉን አመልክተዋል። በድርድሮቹም የግብጽ ተደራዳሪዎች የህዳሴውን ግድብ ላይ ብቻ ሳይሆን፤ በቀጣይ የሚገነቡ ግድቦችን በሚገድብና ከአስዋን ግድብ ጋር በማያያዝ የኢትዮጵያን የመጠቀም መብት ለመግታት ጥረት ማድረጋቸውን ሙሁሩ አስታውሰዋል። እሳቸውም የቴክኒክ ተደራዳሪ ቡድኑ አባል በሆኑበት ድርድር ኢትዮጵያውያን ተደራዳሪዎች የግብጽን የድርድር ሃሳብ በማክሸፍ ድርድሩ በህዳሴ ግድብ ብቻ እንዲመሰረት በማድረግ የአገር ጥቅም እንዳስጠበቁ አመልክተዋል። ለዚህም ዓለም አቀፍ የውሃ አጠቃቀም መርሆዎችን መሠረት በማድረግ ግድቡ በታችኛው የተፋሰስ አገሮች ላይ ጉዳት እንደማያደርስና ተባብረው ከሰሩ ደግሞ ለቀጠናው ኢኮኖሚያዊ እድገት ፋይዳ እንዳለው በማሳየታቸው ለውጥ መምጣቱን ዶክተር አሰግደው ያብራራሉ።
ባለፈው ሳምንት በአሜሪካ የተካሄደው ድርድር የኢትዮጵያን የዓባይ ወንዝ ተጠቃሚነት መብት ያስከበረ መሆኑን አስረድተዋል። ግድቡ 595 ሜትር ከባህር ጠለል በላይ እንዲሞላ ስምምነት መደረሱ የግድቡ 95 ሜትር ከፍታ ውሃ የሚሞላ በመሆኑ ተርባይኖችን በማንቀሳቀስ ኃይል እንዲያመነጭ አስረድተዋል። በዩኒቨርሲቲው የመስኖ ምህንድስና አስተባባሪ ዶክተር ዳኝነት ስልጣን እንዳመለከቱት በድርድሩ የተገኘው ውጤት የግብጽን ተለዋዋጭ ባህሪ በመመከት ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ያረጋገጠ ነው። ግብጽ በውሃ ሙሌቱ ላይ እስከ 21 ዓመታት እንዲራዘም ይዛው የነበረውን አቋም አሁን ኢትዮጵያ ባቀረበችው ከአራት እስከ ሰባት ዓመታት እንዲሆን መስማማቷ የተደራዳሪዎቹን ብቃትና ቁርጠኝነት ያረጋግጣል ብለዋል።
ከድርቅ ጋር ተያይዞ የሚነሳው የውሃ አሞላል ዘላቂ መፍትሄው ኢትዮጵያ እያካሄደች ያለችውን የአፈርና ውሃ እቀባ ሥራን በተፋሰሱ አገሮችም እንዲካሄድ ማድረግ ነው ሲሉም ተናግረዋል። በዚህም የክረምት ዝናብን ወደ መሬት በማስረግ ዓመታዊ ፍሰቱ እንዲጨምር ከማድረግ ባሻገር፤ ግድቡ በደለል እንዳይሞላ በማድረግ ዘርፈ ብዙ ጥቅም ስለሚሰጥ ሁሉም አካላት መደገፍ እንደሚገባ ገልጸዋል። በተጨማሪም ውሃን በቁጠባ በመጠቀምና ጂኦተርማል፣ ፀሐይና ንፋስ ኃይል አማራጮችን ተደራሽ ማድረግም በአማራጭነት መያዝ ይኖርበታል ብለዋል። ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሲጠናቀቅ 145 ሜትር ከፍታ የሚኖረው ሲሆን፣ 74 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ውሃ ይይዛል ተብሎ ይጠበቃል። የግድቡ ግንባታ ለማሳካትም የአገሪቱ ሕዝቦች በቦንድ ግዥና በልገሳ ግድቡን ለመገንባት የሚያስፈልገውን አስተዋጽኦ እያደረጉ ናቸው። ግድቡ ሲጠናቀቅ ለምስራቅ አፍሪካ የኤሌክትሪክ ሃይል በመሸጥ የመሰረተ ልማት ትስስሩን እንደሚያጠናከረው መረጃዎች ያመላክታሉ።