አፍሪካዊያን አገራት እርስ በርስ የጉብኝት ልምድ ሊያዳብሩ ይገባል - ጥምቀትን የታደሙ ጎብኚዎች

42
አዲስ አበባ ጥር 12/2012 አፍሪካዊያን አገራት እርስ በርሳቸው የመጎበኘት ልምድ ሊያዳብሩ እንደሚገባ ከተለያዩ የአፍሪካ አገራት ጥምቀትን የታደሙ አፍሪካዊያን ጎብኚዎች ተናገሩ። ከጎረቤት ኬንያ የመጣው ኢሃራ ኪሃራ በኢትዮጵያ ጥምቀትን ለሁለተኛ ጊዜ ማክበሩን ገልጾ፣ የጥምቀት በዓል አከባበር በየትኛውም ዓለም ከሚገኘው የአደባባይ በዓላት ልዩ ቀለሞች እንዳስተዋለ ይገልጻል። በቀጣይ ዓመት ቤተሰቦቹን ይዞ ለማክበር ማቀዱን የሚገልጸው ኪሃራ በእምነቱ ክርስቲያን መሆኑንና ሙስሊሞች መካ እንደሚሄዱት ሁሉ ጥምቀትን በኢትዮጵያ መታደም ለኔ "መካ እንደመሄድ እቆጥረዋለሁ" ይላል። የጥምቀት ቆይታቸው ያማረና የሰመረ መሆኑን የሚገልጹትና ከምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር ጋና የመጡት ፍራንሲስኮ ደኩ እና ሳንታና በበኩላቸው የሰው ዘር መገኛ ኢትዮጵያን ሁሉም አፍሪካዊ ሊጎበኛት ይገባል ይላሉ። እንግዶቹ አፍሪካዊያን የራሳቸው ባህላዊና ሃይማኖታዊ ማንነት የሚገልጽ ትሁፊታዊ ክዋኔዎች ቢኖሯቸውም፤ ዳሩ እርስ በርስ የመጎበኘት ልምድ እንደሌላቸው አብራርተዋል። ለዚህም የራስን ታሪክ አለማወቅ፣ ጸጋን አለማስተዋወቅ፣ በአገራቱ መካከል ምቹ ትራንስፖስርት ስርዓት አለመኖርና አፍሪካዊ አንድነት ስሜት ማነስ እንደ መንስኤ ይጠቅሳሉ። ስለሆነም አፍሪከዊያን መሪዎች በጉዳዩ ላይ ሊሰሩ ይገባል፣ መገናኛ ብዙሃንም እንደ ጥምቀት አይነት ባህላዊና ሃይማኖታዊ ስርዓቶችን በማስተዋወቅ ጉብኚዎችን መሳብ እንዳለባቸው መክረዋል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም