ጥንታዊ የኢትዮጵያ የዜማ መሳሪያዎች በትምህርት ስርዓት ሊካተት ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ጥንታዊ የኢትዮጵያ የዜማ መሳሪያዎች በትምህርት ስርዓት ሊካተት ይገባል
ጥር 12/2012 (ኢዜና) ጥንታዊ የኢትዮጵያ የዜማ መሳሪያዎች በትምህርት ስርዓት ሊካተት ይገባል ተባለ፡፡ እንደ ቅዱስ ያሬድና አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ አይነት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሊቃውንት ቤተ ክርስቲያኗ ለምህላና ጸሎት የምትጠቀምባቸው የራሷ የሆኑ የዜማ ጥበብ ፈጥረው ለዘመናት እያገለገሉ ይገኛል። ቤተ ክርስቲያን የዜማ ስልቶች ብቻ ሳይሆን የዜማ መሳሪያዎችንም አበጅታ በባህላዊ ሙዚቃዎች መንገድ ጭምር ግልጋሎት እየሰጡ ዘልቀዋል። ለመንፈሳዊ አገልግሎት የሚሰጡ በርካታ የዜማ መሳሪያዎች ዛሬም ድረስ አገልግሎት ላይ ቢገኙም፤ በተለይ ነገሥታት ከቤተ መንግስት እስከ ጦር ሜዳ ሲገለገሉባቸው የነበሩ የዜማ መሳሪያዎች እየተረሱ መጥተዋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ እየተረሱ መምጣት የጀመሩ የቤተ መቅደስና የቤተ ክርስቲያን የዜማ መሳሪያዎች በተለያዩ የአደባባይ ክብረ በዓላት ላይ እየወጡ የብዙሃኑን ትኩረት እየሳቡ ይገኛሉ። ጽን፣ ጽናጽን፣ ከበሮ፣ ዋሽንትና ክራር ቤተ ክርስቲያን ዛሬም ድረስ ለመንፈሳዊ አገልግሎት የምትጠቀምባቸው ሲሆን በገና፣ መለከት፣ ነጋሪት ግን በስፋት አይስተዋሉም። እነዚህ መሳሪያዎች ዘንድሮ በተከበረው በዓለ ጥምቀት በጃንሜዳ ባሕረ-ጥምቀት በስፋት የታዩና የታዳሚያኑን ቀልብ የሳቡ ነበሩ። የሲሳይ የዜማ መሳሪያዎች ማምረቻ ተቋም መስራችና ዋና ስራስኪያጅ አቶ ሲሳይ ደምሴ እንደ ነጋሪት አይነት መሳሪያዎች ኢትዮጵያ ከብሉይ ኪዳን ጀምሮ ከቤተ መቅደስ እስከ ቤተ መንግስት ስትጠቀምባቸው እንደነበር ይገልጻሉ። በማምረቻና ማሰልጠኛ ተቋማቸውም ክራር፣ በገና፣ መለከት፣ ነጋሪት፣ ዋሽንት፣ ጥሩምባ እንደሚያሰለጥኑ፣ ለገበያ እንደሚያቀርቡና በብሔራዊ ከብረ በዓላት ላይ ግልጋሎት እንደሚሰጡ ይናገራሉ። ሌላው በዜማ መሳሪያዎች የስልጠና ማዕከላት ከፍቶ በማሰልጠን ላይ የሚገኘው የማኅበሩ ቅዱሳን አባልና የበገና አሰልጣኝ ዲያቆን ዮሴፍ ከተማ በገና ነገስታት ራሳቸው ጭምር ሲደረድሩበት የነበረ ዘመን ተሻጋሪ መሳሪያ መሆኑን ገልጿል።