በዞኑ የተከሰተውን የአንበጣ መንጋ ለመከላከል ጥረት እየተደረገ ነው

58
ነገሌ ጥር 12/ 2012 (ኢዜና) በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን የተከሰተውን የአንበጣ መንጋ ለመከላከል ጥረት እየተደረገ መሆኑን የዞኑ ግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ጽህፈት ቤት ገለጸ፡፡ በዞኑ መንጋው ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በ10 ወረዳዎች ታይቷል። የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ታደሰ ብዙነህ እንዳሉት በወረዳዎቹ በ13 ሄክታር በግጦሽ ሳርና በተፈጥሮ ደን ላይ ጉዳት ያደረሰውን መንጋ እንዳይስፋፋ እየተሰራ ነው። በዚህም የዞኑ ህዝብ በግብርና ባለሙያዎች እየታገዘ ባህላዊ የመከላከያ መንገዶችን  እየተጠቀመ መሆኑን አመልክተዋል። መንጋው ጉዳት ያደርሳል ተብሎ በተገመተባቸው አካባቢዎች 200 ሊትር ኬሚካል ለመርጨት መዘጋጀቱን ኃላፊው አስረድተዋል፡፡ መንጋው ከሶማሌ ክልል ተነስቶ የጉጂ ዞንን በማቋረጥ ወደ ደቡብ ኢትዮጵያ በመብረር ላይ እንደሆነም አመልክተዋል፡፡ የሀሮ ወላቡ ወረዳ ነዋሪዋ ወይዘሮ አባይነሽ ተስፋዬ መንጋውን በባህላዊ መንገድ ለመከላከል ጥረት እያደረጉ ቢሆንም፤ ከብዛቱና ከሚያደርሰው ጉዳት አንጻር ለመከላከል የመንግሥትን ድጋፍ  ያስፈልገናል ብለዋል፡፡ ለዚሀም የመድኃኒት ርጭት እንዲጠናከር ጠይቀዋል፡፡ አቶ ጉተማ በራጎ የተባሉ ነዋሪ በበኩላቸው የቤት እንስሳት የሚጠቀሙት የግጦሽ ሳርና ቅጠላቅጠል በመንጋው ጉዳት እንደደረሰበት ገልጸዋል፡፡ መንጋውን በባህላዊ መንገድ ሲባረር ከአንዱ ቀበሌ ወደ ሌላ ቀበሌ በመብረር ጉዳት ስለሚያደርስ ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ ይፈልግለት ብለዋል፡፡ በኢትዮጵያ ባለፉት ወራት በተለያዩ አቅጣጫዎች  የአንበጣ መንጋ ተከስቷል። በመንግሥትና በኅብረተሰቡ መንጋውን ለመቆጣጠር በተደረገ  የተቀናጀ ጥረት ውጤት እንደተገኘበት ይታወቃል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም