ዩኔስኮ በኢትዮጵያ ለተመዘገቡ ዓለም አቀፍ ቅርሶች ጥበቃ አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
ዩኔስኮ በኢትዮጵያ ለተመዘገቡ ዓለም አቀፍ ቅርሶች ጥበቃ አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ገለጸ

አዲስ አበባ፣ጥር 12 ቀን 2012 (ኢዜአ) የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ተቋም(ዩኔስኮ) በኢትዮጵያ የተመዘገቡ ዓለም አቀፍ ቅርሶች ተጠብቀው ለቀጣዩ ትውልድ እንዲተላለፉ አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ መሆኑን አስታወቀ።
የጥምቀት በዓል በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ ትናንት በመላ አገሪቷ በተለይም በጃን ሜዳ በድምቀት ተከብሯል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ተቋም(ዩኔስኮ) በኢትዮጵያ ከሚገኙ ቅርሶች ዘጠኝ የሚዳሰሱ፣ አራት ደግሞ ከማይዳሰሱ የዓለም ወካይ ቅርስነት መዝግቧል።
ዩኔስኮ ቅርሶችን የሚመዘግበው አገራት እ.አ.አ በ1972 የሚዳሰሱ ቅርሶችን ለመጠበቅ፤ እ.አ.አ በ2003 ደግሞ የማይዳሰሱ ቅርሶችን ለመጠበቅ በፈረንሳይ ርዕሰ መዲና ፓሪስ የፈረሟቸውን ስምምነቶች መሰረት በማድረግ ነው።
በታህሳስ ወር 2012 ዓ.ም በኮሎምቢያ ርዕሰ መዲና ቦጎታ የተቋሙ የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች ጥበቃ በይነ መንግስታት ኮሚቴ ባደረገው 14ኛ መደበኛ ስብስባው የጥምቀት በዓልን በሰው ልጅ ወካይ የማይዳሰስ ባህላዊ ቅርስነት ለመመዝገብ ውሳኔ ማሳለፉ የሚታወስ ነው።
ዩኔስኮ በኢትዮጵያ ለመዘገባቸው ዓለም አቀፍ ቅርሶች እያደረገ ያለውን ድጋፍ በተመለከተ ኢዜአ የዩኔስኮ አዲስ አበባ ቢሮ የባህል ፕሮግራም ኦፊሰር አቶ ጌቱ አሰፋን አነጋግሯል።
አቶ ጌቱ ዩኔስኮ ቅርሶችን በዓለም ቅርስነት ሲመዘግብ ዋና ዓላማው ቅርሶቹ ተጠብቀው ለትውልድ እንዲተላለፉ ማድረግ እንደሆነ ይገልጻሉ።
ቅርሶች በውስጣቸው የአንድ አገር ባህል፣ እውቀትና እሴት ያካተቱ በመሆናቸው የተጠቀሱት ነገሮች ለቀጣይ ትውልድ መተላለፍ እንዳለባቸው ያምናልም ይላሉ።
በዚሁ መሰረት አገራት ቅርሶቻቸውን ሲያስመዘግቡ ቅርሱን ለመጠበቅና ለሚመጣው ትውልድ ለማስተላለፍ ቃል እንደሚገቡም አመልክተዋል።
በዚሁ መሰረት ኢትዮጵያ ያስመዘገበቻቸው ቅርሶችም እንዲጠበቁ ዩኔስኮ በስልጠናና በባለሙያ የታገዘ ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በዩኔስኮ ቅርስ ሲመዘገብ ቅርሱን የመጠበቅ ዋናው ሃላፊነት የአገሪቷ እንደሆነና አገሪቷ ቅርሱን መጠበቅ በሚያቅታት ወቅት ለዩኔስኮ የድጋፍ ጥያቄ አቅርባ ድጋፍ እየተደረገላት መሆኑንም እነዲሁ።
ዩኔስኮ ቅርሶች ከተመዘገቡ በኋላ የቅርሱ እውቀት፣ ቦታና ቁሳቁሶች በአግባቡ እየተጠበቁ መሆናቸው ላይ ክትትል እንደሚያደርግም ጠቅሰዋል።
ቅርሶች በገንዘብ የማይተመኑ ትልቅ የአገርና የትውልድ ሀብቶች በመሆናቸው ዩኔስኮ ሁልጊዜም ትኩረቱ ቅርሶች ተጠብቀው ለቀጣዩ ትውልድ እንዲተላለፉ ማድረግ ላይ ነውም ብለዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ የተመዘገቡ ቅርሶችን የመጠበቅ ሃላፊነት ዩኔስኮን ጨምሮ የሁሉም የሚመለከተው አካል ሃላፊነት እንደሆነም አክለዋል ኦፊሰሩ።
የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ፣ የጌዴኦ ባህላዊና ተፈጥሯዊ መልክዓ ምድር፣ የመልካ ቆንጡሬ የስነ ምድር የምርምር ስፍራ፣ የድሬ ሼህ ሁሴን መስጊድ፣ የሶፍ ዑመር ዋሻና የትግራይ የተቀደሱ ስፍራዎች መልክዓ ምድር(sacred places of tigray) በኢትዮጵያ ለዩኔስኮ በዓለም የሚዳሰስ ቅርስነት እንዲመዘገቡ ቀርበው ምዝገባቸውን እየጠበቁ ያሉ ቅርሶች ናቸው።
የዩኔስኮ አዲስ አበባ ቢሮ የባህል ፕሮግራም ኦፊሰር አቶ ጌቱ አሰፋ የተለያዩ አገራት በየዓመቱ ብዙ ቅርሶች እንዲመዘገቡላቸው ጥያቄ ስለሚያቀርቡና የቅርሱ መመዝገብ ተገቢነት ለመመልከት ጊዜ የሚፈጅ በመሆኑ አንድ አገር በአንድ ዓመት ውስጥ ማስመዝገብ የሚችለው አንድ ቅርስ ብቻ እንደሆነም ገልጸዋል።
የዩኔስኮ ኃላፊነትም ቅርሶች እንዲመዘገቡ ሲቀርብለት ግምገማ አድርጎ መመዝገብ እንደሆነና ቅርሶችን በዚህ ጊዜ ይመዝገቡልኝ የማለትና የማስመዝገብ ሃላፊነት የአቅራቢው መንግስት አካል ሃላፊነት ነው ብለዋል።
የአሸንዳ፣ ሻደይ፣ አሸንድዬና ሶለል በዓል በዩኔስኮ የማይዳሰስ ቅርስ ሆኖ እንዲመዘገብ የተዘጋጀው የማስመረጫ ሰነድ ማስተካካያ ተደርጎበት በመጋቢት ወር 2012 ዓ.ም ለዩኔስኮ ለሁለተኛ ጊዜ እንደሚላክ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን በታህሳስ ወር 2012 ዓ.ም ለኢዜአ መግለጹ የሚታወስ ነው።