ሰላምን የማስከበር ጉዳይ የዕለት ተግባራቸው እንደሚያደርጉት የባህር ዳር ከተማ ወጣቶች ተናገሩ - ኢዜአ አማርኛ
ሰላምን የማስከበር ጉዳይ የዕለት ተግባራቸው እንደሚያደርጉት የባህር ዳር ከተማ ወጣቶች ተናገሩ
ባህር ዳር፣ጥር 12 ቀን 2012 (ኢዜአ) ሰላምን የማስከበር ጉዳይ በሃይማኖታዊና ህዝባዊ በዓላት ብቻ ሳይሆን፣ የዕለት ተግባራቸው እንደሚያደርጉት የባህር ዳር ከተማ አንዳንድ ወጣቶች ገለጹ። ወጣቶቹ በከተማዋ የተከበረውን የጥምቀትን በዓል የጥበቃ ሥራ አስተባበረዋል። ወጣቶቹ በሰጡት አስተያየት የኅብረተሰቡን ሰላምና ደህንነት ማስከበር ተግባር፤በበዓላት ወቅት ብቻ ሳይሆን፤የዕለት ሥራቸው አካል ያደርጉታል። ወጣት ባሻህ ደምሴ እንደገለጸው የከተማዋን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ አስተባባሪና ቀስቃሽ ሳያስፈልጋቸው ከአካባቢው ወጣቶች ጋር ተባብረው እየሰሩ ነው። በሁሉም አካባቢዎች ሰላምና ደህንነትን የሚረጋገጠው እንደ ግለሰብም ሆነ እንደማህበረሰብ በተናጠልና በጋራ ሁሉም ኃላፊነቱን ሲወጣ መሆኑንም ገልጿል። ሰላም ለአገር ልማት፣ ብልጽግናና እድገት ፋይዳው ጉልህ መሆኑን የተናገረው ባሻህ፣ለሰላምና ደህንነት ዘብ መቆም ከሁሉም በላይ ጥቅሙ ለራስ ነው ብሏል። በዚህም የጥምቀት በዓልን ጨምሮ በሌሎች ሃይማኖታዊና ህዝባዊ በዓላት ላይ በየዓመቱ ሰላምን በማስከበር ስራ እንደሚሰማራ አውስቷል። በዚህ ዓመትም በተመሳሳይ መልኩ ኅብረተሰቡን ማገልገሉን አስታውቋል። ''ሰላምን የማሰከበር ጉዳይ ለጸጥታ አካላት ብቻ ሊተው የሚገባ አይደለም" ያለው ደግሞ ሌላኛው የከተማዋ ነዋሪ ወጣት አቡሸት ጎበዜ ነው። የአገር ሰላምና ደህንነት የሚከበረው ኅብረተሰቡ በአካባቢው ከሚገኘው የጸጥታ ኃይል ጎን በመሰለፍ የአካባቢውን ሰላም ለማስከበር ሲሰራ ነው የሚል እምነት እንዳለው ገልጿል። "ይህን በመገንዘቤም በሃይማኖታዊና ህዝባዊ በዓላቶች ላይ ሰላምን ለማስከበር በበጎ አድራጎት ስራ መስራት ከጀመርኩ ከአምስት ዓመታት በላይ ሆኖኛል" ብሏል። በየዓመቱ ለጥምቀት በዓል ዝግጅት የሚደረገው ሰላምን የማስከበር እንቅስቃሴ ወጣቱ እርስበርስ በመተዋወቅና በመተሳሰር ለመልካም ተግባር በእንድ ላይ እንዲሰለፍ እንዳደረገው ወጣት ትዕግስት ሙሉቀን ገልጻለች። ይህም ከጥንት ጀምሮ ሲከወን የመጣውን ሃይማኖታዊና ባህላዊ እሴት ተጠብቆ ለትውልድ እንዲተላለፍ ወጣቱ ድርሻውን ለመወጣት እንዳስቻለው ተናግራለች። በተለይም የዘንድሮው የጥምቀት በዓል የዓለም ቅርስ ሆኖ በተመዘገበ ማግስት በመከበሩ እርሷና ጓደኞቿ በዓሉ በሰላም እንዲጠናቀቅ በቁርጠኝነትለመስራት አስችሎናል ብላለች። የጥምቀተ በዓል ትናንት በመላው ኢትዮጵያ መከበሩ ይታወሳል።