ቀጥታ፡

ባህልና እሴቶችን አክብረንና ጠብቀን ለትዉልድ ለማሸጋገር ድርሻችንን እንወጣለን- የደሴ ወጣቶች

ደሴ ጥር 11 ቀን 2012 ባህልና እሴቶቻችንን በመጤ ባህል ሳይበረዙ አክብረንና ጠብቀን ለትዉልድ ለማሸጋገር ድርሻችንን እንወጣልን ሲሉ የጥምቀት በዓልን ያከበሩ የደሴ ከተማ ወጣቶች ተናገሩ። ጥምቀት በተለያዩ ሐይማኖታዊ ክዋኔዎች በደሴ ከተማ እየተከበረ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልገሎት በከተማው በዓሉን ሲያከብሩ ያነጋገራቸው ወጣቶች እንደተናገሩት ከአባቶች የተወረሰሱትን ባህልና እሴቶች ወደ ቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ ሚናቸውን ይወጣሉ።

የከተማው ነዋሪ ወጣት ሰለሞን ዓሊ ኢትዮጵያ ሕዝቡን እርስ በእርስ የሚያስተሳስሩ ባህልና እሴቶች ያላት አገር መሆኗን አመልክቶ፣ባህልን ከብረዛና ከጥፋት ለመታደግ ድርሻችን እንወጣለን ብሏል።

በዓሉ ሃይማኖታዊና ባህላዊ እሴቱን ጠብቆ በሰላማዊ መንገድ እንዲከበር በተደራጀ አግባብ ከፀጥታ መዋቅሩ ጋር  በመሥራት ላይ  መሆናቸውን አስታውቋል።

ሌላው የከተማዋው ነዋሪ ወጣት ተስፋዬ እምሩ በበኩሉ እየተሸረሸረ የመጣውን ኢትዮጵያዊ አንድነት፣ ፍቅርና መከባበር ለመመለስ ከሌሎች ወጣቶች እየሰራን ነው ብሏል፡፡

በዓላትን ከሌሎች እምነት ተከታዮች ጋር  በአንድነትና በፍቅር እያከበሩ ባህልና እሴቶችን ለማስቀጠል የጀመሩትን ጥረት እንደሚያጠናክርም ገልጿል፡፡

ወጣት ኻሊድ የሱፍ የተባለ ነዋሪ በበኩሉ የከተማው ወጣቶች የክርስትናም ሆነ የእስልምና በዓላትን በጋራ እንደሚያከብሩ አስታውሷል፡፡

የጥምቀት በዓልን በሆታና በእልልታ በጋራ እያከበሩ መሆኑን ገልጾ፣ በዓሉ ምቹ ለማድረግ የተለያዩ አካባቢዎችን ከሁለት ቀናት በፊት ማጽዳታቸውን ገልጿል፡፡

"ወሎ አባቱ ሙስሊም ቢሆን እናቱ ወይም እህት ወንድሞቹ ክርስቲያን ናቸው ያለው" ወጣት ኻሊድ፣ እሱም የክርስትና እምነት ተከታይ ቤተሰቦች እንዳሉት ተናግሯል፡፡

የደቡብ ወሎ ዞን አገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ ሊቀ መምህራን ብርሃነ ህይወት እውነቱ በበኩላቸው በዓሉ በፍቅር፣ በደስታ፣ በአንድነትና በመተሳሰብ እየተከበረ ነው።

"ወሎን በሐይማኖትም ሆነ በብሔር መለያየት አይቻልም ያሉት" ሥራ አስኪያጁ፣ ወጣቱ የአባቶችን አንድነትና መከባበር ለማስቀጠል የጀመረውን ጥረቱን እንዲያጠናክር ጠይቀዋል፡፡

በዓሉ በሰላም እንዲጠናቀቅ ከሁለት ሺህ በላይ ወጣቶች ተደራጅተው ከጸጥታ ኃይሉ ጋር በቅንጅት እየሰሩ ነው ብለዋል፡፡

በዓሉ በደሴ ከተማ ባህላዊና ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን ተከትሎ በሰላማዊ መንገድ እየተከበረ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም