ቀጥታ፡

ጥምቀተ-ባህሩን ከቅርስነቱ ባለፈ አስተምህሮውንም ሁሉም ሊጠቀም ይገባል ...የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ-ክርስቲያን

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 11/2012 የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ-ክርስቲያን የባህረ-ጥምቀቱ ለሰዎች ሁሉ በቅርስነቱ ከሚሰጠው በተጨማሪ አስተምህሮውም ለሠላም፣ ለሀገር አንድነትና ገጽታ ግንባታ አበርክቶውን ሁሉም መጠቀም እንደሚያስፈልግ ተገለጸ። ቤተ-ክርስቲያኗ በዓሉ በዓለም ቅርስነት መመዝገቡን ተከትሎ ስርዓተ-ጥምቀቱን በአዲስ አበባ አክብራለች። በዓሉ በዓለም ቅርስነት በመመዝገቡ ከሚሰጠው ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው በተጨማሪ ባህላዊና ሃይማኖታዊ ይዘቱን በጠበቀ አስተምህሮውን መጠቀም እንደሚገባ ካህናቱና ምዕመኑ አስረድተዋል። ስለሆነም የክርስቶስን አስተምህሮ ለሰዎች መንፈሳዊ ዕድሳት፣ ለገጽታ ግንባታ፣ ለሠላም እንዲሁም ለአንድነት መጠቀም ይገባል ያሉት በቤተ ክርስቲያኗ የብጹዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ተወካይ አባ ተሾመ ፍቅሬ ናቸው። የካቴድራሉ ቆሞስ አባ ታምራት ጥዑም በበኩላቸው፤ጥምቀቱን አስመልክቶ ክርስቶስ የመጣበትን ዓላማና አስተምህሮ መረዳት ለሰዎች ግለሰባዊና የእርስ በርስ አኗኗር በቂ ነው ይላሉ። እንዲሁም በዓሉ በቅርስነት መመዝገቡ አስፈላጊነቱን ለሰዎች ሁሉና በተለይም ኢትዮጵያውያንን በሙሉ  የእምነቱና የቅርሱ ባለቤት ያደርጋል የሚትለው ደግሞ የበዓሉ ታዳሚ ራሔል አለሙ ነች። ራሔል እንደምትለው በዓለም ቅርስነቱም ለአገራችን የቱሪዝም ፍሰትን ስለሚጨምር የጋራ አገራዊ ጥቅምን  ያረጋግጣል። ስለሆነም በቅርስነቱ የተሰጠው አለም አቀፍ እውቅና ቀጣይነት እንዲኖረውም  ምዕመኑ ብቻ ሳይሆን ሁሉም ማህበረሰብ ባህላዊ ይዘቱን ሳይለቅ እንዲጠብቅ አባቶቹና ምዕመናኑ አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም