ቀጥታ፡

በጎንደር ከተማ በተከበረው የጥምቀት በዓል ከ15 ሺህ በላይ የውጭ ዜጎች ተገኝተዋል

ጎንደር  (ኢዜአ) ጥር 11/2012 በጎንደር ከተማ እየተከበረ ባለው የጥምቀት በዓል ከ15 ሺህ በላይ የውጭ ዜጎች መገኘታቸውን የጎንደር ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም መምሪያ አስታወቀ፡፡

ኢትዮጵያ ካሏት የቅርስ ሀብቶች ባሻገር የህዝቦቿ እንግዳ አክባሪነት ቱሪስቶችን የመሳብ የላቀ አቅም አለው ሲሉ ጥምቀትን በጎንደር ለመታደም የመጡ የውጭ ዜጎች ተናገሩ፡፡

በመምሪያው የቅርስ ጥበቃና ቱሪዝም ልማት ቡድን መሪ አቶ አይቸው አዲሱ ለኢዜአ እንደገለፁት የጥምቀት በዓል በማይዳሰስ ቅርስ መመዝገቡ የውጭ  ቱሪስቶች ቁጥር እንዲጨምር አድርጓል።

ለቱሪስቶቹ ቁጥር መጨመርም ጥምቀት  በማይዳሰስ ቅርስነት ከመመዝገቡ ባለፈ በአካባቢው አንፃራዊ ሰላም መስፈኑ አስተዋጽኦ ማበርከቱን አመልክተዋል።

ከዚህ በፊት በበዓሉ ከ8 ሺህ የማይበልጥ የውጭ ዜጎች ይታደሙ እንደነበር አስታውሰው፤በዚህ ዓመት ግን በበዓሉ የታደሙት ከእጥፍ በተጠጋጋ ቁጥር መጨመሩን ተናግረዋል።

ይህም ለቀጣይ የቱሪዝም ልማትና እድገት አዎንታዊ አስተዋፅኦ እንዳለው አመልክተዋል።

የቱሪስቶች ቁጥር መጨመርም የከተማዋን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እንዲነቃቃ ማገዙን የጠቆሙት ቡድን መሪው፣ ከቱሪስቶቹ ብቻ ከ28 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ከተማዋ ታገኛለች ብለዋል።

በዓሉን ለማክበር የመጡ እንግዶች የሆቴልና የመኝታ አገልግሎት እጥረት እንዳይገጥማቸውም የግል ቤቶችን ጊዜያዊ የመኝታ አገልግሎት እንዲሰጡ መደረጉን ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም አንዳንድ የመንግሥት ተቋማትም ለእንግዶቹ የመኝታ አገልግሎት መስጠታቸውን አቶ አይቸው አስታውቀዋል፡፡

የከተራና የጥምቀት በዓል በጎንደር ያለው አከባበርም የተለየ ደስታ እንደፈጠረባቸው የገለፁት ደግሞ ከጀርመን የመጡት ሀንስ ስቴፈን ናቸው።

ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ለሁለተኛ ጊዜ እንደሆነ ጠቅሰው፤አገሪቱ ካሏት የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶች በተጨማሪ የህዝቦቿ እንግዳ አክባሪነት አድናቆት ይገባዋል ብለዋል፡፡

ከከተራው ጀምሮ ዛሬ እየተከበረ ባለው የጥምቀት በዓልም ልዩ ደስታን የሚፈጥሩ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ትዕይንቶች እንደተመለከቱ ገልጸው፤ ሌሎች ይህን ድንቅ ባህልና ሕዝብ ያላዩ ወዳጅ ዘመዶቻቸው ወደዚህ መጥተው እንደሚያደርጉም  ገልጸዋል፡፡

ሌላኛውና ከአራት ቀን በፊት ወደ ጎንደር እንደመጣ የተናገረው ቤልጅየማዊው ሉካስ ሊያም በበኩሉ ''የህዝቡ እንግዳ አቀባበልና አክብሮት የኢትዮጵያ ሌላኛው የቱሪዝም ሀብት ምንጭ ነው'' ይላሉ፡፡

‹‹የፋሲል ቤተ መንግሥትን ለመጎብኘት ነበር መጥቼ የነበረው። ነገር ግን ከበዓሉ በፊት በነበረው የጎዳና ላይ ልዩ ልዩ ትርዒቶች ተማርኬ ጥምቀትንም ታድሜ ለመሄድ ወሰንኩኝ፤›› ያሉት ጎብኚ፣ የከተራና የጥምቀት በዓላት አከባበር ሥርዓትን ''አስደሳች'' በማለት ገልጸውታል።

የጥምቀት በዓል አከባበር "ከጠበቅኩት በላይ ነው የሆነብኝ። በዓለም ቅርስ መመዝገቡ ትክክለኛ ነው እያልኩ እስካሁን መዘግየት አልነበረበትም" ያለችው ደግሞ ስፔናዊቷ ጇን ካሚላ ናት፡፡

የወጣቶች ባህላዊ አለባበስ፣ አጨፋፈርና መንፈሳዊ መዝሙሩ ቀልብን የሚስብና ማራኪ እንደሆነም ገልፃለች።

በበዓሉ 2 ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ እንደታደመ ከመምሪያ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም