የጥምቀት በዓል በመላ ሀገሪቱ በደማቅ ሁኔታ እየተከበረ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የጥምቀት በዓል በመላ ሀገሪቱ በደማቅ ሁኔታ እየተከበረ ነው
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 11/2012 በአዲስ አበባ ጃን ሜዳ ለኃይማኖቱ ተካታዮች መልዕክት ያስተላለፉት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በዓሉ የፍቅርና የአንድነት ተምሳሌት እንደሆነ አስታውቀዋል። ይህም በመሆኑ በዓሉ በመከባበር ሊከበር እንደሚገባ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። ሊቀ ጳጳስ አቡነ ማትያስ ''እግዚያብሔር ከሰው ልጆች የሚፈልገው እጅግ ቀላልና ዋጋ የማያስከፍል ሲሆን እሱም ፍቅር ነው'' ብለዋል። "ፍቅር ምቾትን፣ ደስታን፣ መዋደድን፣ የምታጎናጽፍ ምቹ ህይወት በመሆኗም በፍቅር ውስጥ ያለ ሰው ልበ ሙሉነትና ደፋር ነው" ሲሊም ጠቅሰዋል ። "በፍቅር መኖር ከነጻነትና በነጻነት ከመኖር በላይ ነው"፤ ስለሆነም የሰው ልጆች በፍቅር ይኖር ዘንድ መልዕክት አስተላልፈዋል። በክብረ በዓሉ ላይ በእንግድነት ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ ''የዓለም ቅርስ የሆነውን በዓል የመንከባከብና የመጠበቅ ግዴታ አለብን'' ነው ያሉት። ምክትል ከንቲባው በዓሉ ትውፊታዊ እሴቱ ተጠብቆ ለትውልድ ይተላለፍ ዘንድ ከተማ አስተዳደሩ በቅርበት ድጋፍ ያደርጋልም ብለዋል። በተመሳሳይ ሌሎች በዓሉ ላይ የታደሙ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ለሕዝበ ክርስቲያኑ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል። የጥምቀት በዓል በድምቀት ከሚከበርባቸው ቦታዎች አንዱ በሆነው የጎንደር ከተማ የኢፌድሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በተገኙበት በድምቀት እየተከበረ ነው። በዓለም ወካይ ቅርስነት በቅርቡ የተመዘገበው ጥምቀት በመላው የሀገሪቷ አካባቢዎችም ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ እየተከበረ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።