የጥምቀት በዓልን ስናከብር ለሰላም መረጋገጥ የድርሻችንን ለመወጣት ቃል በመግባት ነው…የኃይማኖት አባቶች - ኢዜአ አማርኛ
የጥምቀት በዓልን ስናከብር ለሰላም መረጋገጥ የድርሻችንን ለመወጣት ቃል በመግባት ነው…የኃይማኖት አባቶች
አዳማና ፍቼ ኢዜአ ጥር 11/2012 የጥምቀት በዓልን ስናከብር ንሰሀ በመግባትና ለሰላማችን ቀጣይነት በጋራ በመስራት ሊሆን እንደሚገባ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የኃይማኖት አባቶች ገለጹ። በዓሉ በአዳማ እና በፍቼ ከተሞች የእምነቱ ተከታይ ምዕመናን የኃይማኖት አባቶችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በተሳተፉበት እየተከበረ ይገኛል። የምስራቅ ሸዋ ዞን ሀገረ ስብከት ሊቀዻዻስ አቡነ ጎርጎሪዮስ በአዳማ ከከተራው ጀምሮ ለምዕመናን ባስተላለፉት መልዕክት ህዝበ ክርስቲያኑ በዓሉን ሲያከብር ዘርና ቀለም ሳይለይ በአንድነት ከሌሎች ወገኖቹ ጋር ሆኖ ለሃገሩ ሰላም መረጋገጥ መስራት ይኖርበታል። "በዓሉ ህዝብን ያቀራርባል፣የመረዳዳት ባህልንም ያሳድጋል" ያሉት ሊቀ ዻዻሱ በአሉን ስናከበር እራሳችንን ቆም ብለን በማየት ንሰሀ የምንገባበትና ለሰላማችን ቀጣይነት አስተዋጽኦ የምናደርግበት ሊሆን ይገባል" ብለዋል፡፡ የበአሉ ታዳሚዎች በሌላውም ጊዜ እርስ በእርስ በመዋደድ፣በመፈቃቀር፣ በመቻቻልና በመከባበር በአብሮነት ዘብ እንዲቆሙ ጥሪያቸውን አስተላልፈው እምነትን በነጻነት ማራመድ የሚቻለውም ሰላም ሲኖር ብቻ በመሆኑ አመልክተዋል። ከባዕሉ ታዳሚዎች መካከል አቶ አዱኜ ቀልቤሳ በሰጡት አስተያየት በበዓሉ ላይ የሚካሄደው ሃይማኖታዊ ትዕይንት ማራኪና ላቅ ያለ ትርጉም የሚሰጠው በመሆኑ በየዓመቱ በዓሉን በናፍቆት በመጠበቅ ያከብሩታል። "በአሁኑ ወቅት በእምነት ሽፋን ቤተክርስቲያንና መስጂድ የሚያቃጥሉ እንዲሁም የተለያዩ አጀንዳዎችን ለማራመድ የሚንቀሳቀሱ አካላት ስለሚታዩ መንግስትና የእምነት አባቶች ለሚያስተላልፉት መልዕክት ጆሮ መስጠት ያስፈልጋል” ያለው ደግሞ ወጣት እሸቱ ዲነግዴ ነው። በተመሳሳይም በፍቼና አካባቢው የበዓል አከባበር ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሰሜን ሸዋ ዞን ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቀዎስጦስ በዜጐች መካከል ሰላም፣ ወንድማማችነትና አንድነት እንዲጐለብት መቻቻል እንደሚያስፈልግ አስተምረዋል። "በአሉን በአንድነት ተሰብስበን ማክበራችን ያስደስታል" ያሉት ጳጳሱ ምዕመናን ሀይማኖታቸውን ለመጠበቅ ከሚያደርጉት እንቅስቃሴ ጐን ለጐን ለሰላም ለወዳጅነትና ለፍቅር መክፈል ያለባቸውን ትልቅ ዋጋ ለመክፈል መዘጋጀት እንዳለባቸው አሳስበዋል። የከተማው ነዋሪ መጋቢ ናትናኤል ሀብተማርያም የሀገር ታሪክና የማንነት መገለጫ የሆኑ ኃይማኖታዊና ባህላዊ እሴቶችን በተግባር በመተርጐም ከሌሎች ጋር በመሆን በዓሉን እያከበሩ መሆኑን ተናግረዋል። ከተማዋን በማስዋብ እንግዶችን በአግባቡ ለማስተናገድ ከወጣቶች ጋር የፀጥታን ስራ ጨምሮ የቱሪዝም ሀብትን የማስተዋወቅ ስራ እየሰሩ መሆኑን የተናገሩት የከተማው ከንቲባ አቶ አስመራው አደሬ ናቸው። "በአሉ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች የቆዩ እሴቶቻቸውን የሚያንፀባርቁበት፣ የሚተዋወቁበትና የሚለዋወጡበት መድረክ በመሆኑ የአንድነት መሰረታችንን በማጠናከር የመግባባትና የመተማመን መንፈስ ይዘራል" ብለዋል። የጥምቀት በዓል ዘንድሮ በተባበሩት መንግስታት የትምህርት የሳይንስና የባህል ድርጅት /UNESCO/ የማይዳሰስ የዓለም ቅርስነት ከተመዘገበ በኋላ እንደመከበሩ ከተለያዩ ሃገራት የገቡ ቱሪስቶችና ምዕመናን በተገኙበት በመላው ሃገሪቱ እየተከበረ ይገኛል።